
ባሕር ዳር የተፈጥሮ ልግስና እና ባሕል በጥበብ የተሳሰሩባት፣ የቅርስ እና የታሪክ ማኅደር፣ የዓባይ እና ጣና ንግሥት ውብ ከተማ ናት። በከተማዋ የሚካሄደውን አህጉር አቀፍ የጣና የፎረም መድረክ ለማካሄድ ሽር ጉዷን ጨርሳ እንግዶቿን በመቀበል ላይ ትገኛለች። ይህም ከተማዋን ለዓለም
በማስተዋወቅ የቱሪዝም ኢንዱስትሪውን በከፍተኛ ሁኔታ የሚያነቃቃ መድረክ ነው። በዚሁ መድረክ ከተማዋን የሚወክሉ የባሕል አልባሳት፣ የዕደ ጥበብ ውጤቶች እና የማኅበረሰቡ የእንግዳ ተቀባይነት እሴት ጎልቶ በስፋት ይተዋወቃሉ።
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ባሕል፣ ቱሪዝም እና ስፖርት መምሪያ ኀላፊ ጋሻው እንዳለው በከተማዋ ለሚካሄደው የጣና ፎረም የእንግዶችን ቆይታ ስኬታማ እና ምቹ ለማድረግ የሚያስችሉ ዝግጅቶች በቅንጅት ተጠናቅቀዋል ብለዋል። በፎረሙ የአፍሪካ ከፍተኛ መሪዎች፣ ዲፕሎማቶች፣ አምባሳደሮች እና የሲቪል ማኀበረሰብ ተወካዮች ይሳተፋሉ ተብሎ ይጠበቃል።
የከተማዋን የሆቴል ቱሪዝም ለማነቃቃት እና ባሕር ዳርን የቱሪዝም ኮንፈረንስ ማዕከል ለማድረግ ትልቅ ዕድል የሚፈጥር ነውም ብለዋል። በቅድመ ዝግጅት ሂደቱ ሆቴሎች የውስጥ አገልግሎቶቻቸውን ማሟላታቸው መረጋገጡን ነው የገለጹት። ከዚህ በተጨማሪም ተጓዳኝ የአገልግሎት
ዘርፎችን ለማቀላጠፍ ከጀልባ አሽከርካሪዎች፣ አስጎብኚዎች እና ከኤርፖርት ታክሲ አገልግሎት ሰጪዎች ጋር ተቀናጅቶ ለመሥራት ለባለሙያዎቹ እና ለአገልግሎት ሰጪ አካላት የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮች ስለመፈጠሩ ነው ያስረዱት። እንግዶችን በፍቅር ለመቀበል እና አስተማማኝ
የመስተንግዶ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል በቂ ዝግጅት ተደርጓል ነው ያሉት። በፎረሙ የሚታደሙት እንግዶች በቆይታቸው ደስተኛ ኾነው እንዲያሳልፉ መሠራቱን ያነሱት መምሪያ ኀላፊው ሀገር በቀል የምግብ፣ የስጦታ እና የባሕል ምርቶችን በቀላሉ የሚያገኙበት ምቹ ሁኔታ
ተፈጥሯል ብለዋል። ከዚህ ጎን ለጎን ከተማዋን ሙሉ በሙሉ ለዕይታ ዝግጁ የማድረግ ሥራ ተሠርቷል ብለዋል። በአጠቃላይ የከተማዋን ተፈጥሮአዊ እና ዘመናዊ ውበት በመግለጥ ለእንግዶች ፍጹም ምቹ እና ሳቢ አካባቢ ተፈጥሯል። ይህ ታላቅ ፎረም የባሕር ዳርን መልካም ገጽታ ለዓለም ለማስተዋወቅ እና ከተማዋን የኮንፈረንስ ቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ በሚደረገው ጥረት ውስጥ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረውም ተገልጿል።
በሥራውድንቅ ደሳለው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
