
በሰፋፊ ጎዳናዎች የሚስተጋባው የጽናት፣ የነጻነት እና የአንድነት ድምጽ የአየር ንብረቱን ተቆጣጥሮታል። በአማራ ክልል በተለያዩ ከተሞች እና ገጠራማ አካባቢዎች አደባባይ የወጣው ሕዝብ ያስተጋባው መፈክር ተራ የቃላት ስብስብ አይደለም፤ የዕለት ከዕለት ሕይወቱ በሰላም እንዲቃኝ፣
ልጆቹ ሰላም ውለው እንዲገቡ፣ አልምቶ የማደግ ህልሙ እና ነገን በፍቅር የመኖር ተስፋው በነጻነት እንዲታጀብ የሚሻ የልብ ጥልቅ ስሜት እንጂ።
ይህ ታላቅ ሕዝባዊ ትዕይንት የሕዝቡ የሰላም ጥማት በግልጽ የታየበት ነው። ማኅበረሰቡ የዕለት ከዕለት ኑሮውን የሚያናጋው፣ የእርስ በእርስ
ፍቅርን የሚሸረሽረው እና የልማት በሩን የሚዘጋው ዕኩይ ተግባር አላስችለው ብሎ በአንድ ድምጽ አደባባይ ወጥቷል። የሀገርን ህልውና ለመሸጥ ከውጭ ጠላቶች እና ከታሪካዊ ሴረኞች ጋር የሚሰለፉ የጥፋት ኃይሎችን እና የባንዳዎችን ሴራ በጽኑ ያወገዘው ሕዝቡ በደሙ እና በአጥንቱ ዋጋ
እየከፈለ ለሚገኘው የሀገር መከላከያ ሠራዊት እና ለክልሉ የጸጥታ ኃይሎች ያለውን አክብሮት እና አለኝታነትም በተግባር ደጀንነቱ አረጋግጧል።
በየአደባባዩ ከተደመጡት የሕዝብ ብሶቶች እና ተስፋዎች እኩል የሠራዊቱ ተጋድሎ በሁላችንም ጓዳ የሚፈጥረው ሰላም ጎልቶ ታይቷል።
ይህ የሕዝብ ድምጽ እንደሚያስረግጠው ሰላም ማለት የጦር መሣሪያ ዝምታ ብቻ ሳይኾን የወላጅ እፎይታ፣ የሕጻናት ፈገግታ እና የገበሬው የተረጋጋ መስተጋብር ነው።
ሰላም የልማት እና የሉዓላዊነት መሠረት መኾኑን የተገነዘበው የአማራ ሕዝብ የነገዋን የበለጸገች ኢትዮጵያ ስዕል በልቡ ስሎ አደባባይ ወጥቷል።
“ሀገርን ለማጽናት እና ለማበልጸግ ከመንግሥት ጎን እንሰለፋለን” ያለው ሕዝቡ ታላቁን የሕዳሴ ግድብ ማጠናቀቅ ብቻ ሳይኾን አሕጉራዊ የኢኮኖሚ ጥንካሬውን የሚያረጋግጥበትን የባሕር በር ጥያቄም በጽናት ደግፏል።
“ሕዝባችን እውነተኛ ፍላጎቱ ሰላም፣ የሕግ የበላይነት እና ልማት የተረጋገጠበት ሀገር እና ክልል መፍጠር ነው ብለዋል። ሕዝቡ ባደረገው ከፍተኛ ትዕይንተ-ሕዝብ በተግባር ያረጋገጠውም ይህንኑ ነው። ከዚህ በተጨማሪም ለሀገራችን አንድነት ያለውን የማይናወጥ አቋም በድጋሜ የገለጸበት እንደኾነም ርእሰ መሥተዳድሩ ገልጸዋል።
የአማራ ክልል ሕዝብ የሰላም፣ የእድገት እና የኅብረ-ብሔራዊ አንድነት ማሠሪያ እንጂ የጥፋት እና የሴራ መጫወቻ ሊኾን እንደማይችል ሕዝባዊ ሰልፉ ግልጽ መልዕክት አስተላልፏል።
የትኛውም የውስጥ ባንዳም ኾነ የውጭ ጠላት ዕኩይ ሴራ የኢትዮጵያን የጋራ እድገት እና የተስፋ መንገድ ማስተጓጎል እንደማይችል ለዓለም ያበሰረበት አጋጣሚ ኾኖም አልፏል።
ዘጋቢ፦ ቴዎድሮስ ደሴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
