
የአማራ ክልል ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ኀላፊ እሸቱ የሱፍ (ዶ.ር) ባለፉት ዓመታት የጸጥታ ኃይልን በመገንባት እና ስምሪት በመስጠት ስኬቶች ተመዝግበዋል ብለዋል።
የሰላም አስከባሪዎችን እና ሚሊሻዎችን በማደራጀት እና ለግዳጅ ብቁ የኾኑ የጸጥታ ተቋማትን በመፍጠር የጸጥታ ሥራው ከፍተኛ መሻሻል እንዳሳየ አመላክተዋል።
የውጪ ጠላቶች ውስጣዊ ኃይሎችን በማስተባበር ክልሉን የማተራመስ እና ሀገር የማፍረስ ዕቅድ ይዘው ቢንቀሳቀሱም ሀሳባቸው ከንቱ እንደቀረ ተናግረዋል። የጸጥታ መዋቅሩ የሕግ የበላይነትን የማስከበር ሥራ በተሳካ ሁኔታ በማከናወን ላይ እንደኾነም አንስተዋል።
ሕዝቡ የሕገ ወጥ ታጣቂዎችን ትርክቶች በመረዳት ልማት እና ሰላም እንዳይቋረጥ እየተቃወመ ነው ብለዋል። በሰልፎች ጭምር “የሕግ የበላይነት ይከበር፣ ጽንፈኝነት ይቁም፣ ሀገር ለማውደም እና ለማፍረስ የሚደረግን የተላላኪነት እንቅስቃሴ አንቀበልም” በሚል ሰላም ፈላጊነቱን እያረጋገጠ ስለመኾኑ ጠቁመዋል። ለጸጥታ ኃይሉ ያለውን ደጀንነትም በተግባር እየገለጸ ነው ብለዋል።
በቀጣይ የሕግ የበላይነትን ማስከበር ላይ ትኩረት ተደርጎ ይሠራል ነው ያለት። ሰላምን ማዕከል ማድረግ፣ የሕዝቡን አጋዥነት እና የሰላም ባለቤት ማሳደግ ሌላው ቁልፍ ጉዳይ ይኾናል ተብሏል።
የጸጥታ መዋቅሩን ማጠናከር እና የጠላትን ዕቅድ በማክሸፍ እያንዳንዱ አካባቢ አስተማማኝ ሰላም የሚያገኝበት ሁኔታ መፍጠርም የቀጣይ የትኩረት አቅጣጫ ኾኗል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
