ሰሚ የሌለው የግብጽ ጩኸት እና የማይገታው የኢትዮጵያ ጉዞ

12
ግብጽ እንደ ሀገር ከተመሠረተችበት ጊዜ ጀምሮ የዓባይ ወንዝን በብቸኝነት ስትጠቀምበት ኖራለች። ብቸኛ ተጠቃሚነታቸውን የህልውና ጉዳይ አድርገው በመያዝ ለዜጎቻቸውም ያልተገባ የሥነ ልቦና ትርክትን ገንብተውበታል። በዚህም የዓባይ ወንዝ የበላይ ጠባቂነትን እና ብቸኛ ተጠቃሚነታቸውን የውጭ ፖሊሲ ማጠንጠኛቸው አድርገውት ቆይተዋል።
ከአሚኮ ጋር ቆይታ ያደረጉት የታሪክ ተመራማሪው ፕሮፌሰር አየለ በክሬ ግብጽ የዓባይን ወንዝ መሠረት አድርጋ ባፈራችው ሃብት፣ በመሠረተችው ሀገረ መንግሥት እና በገነባችው ሥነ ልቦና በአፍሪካ ታላቅ ሀገር እንደኾነች አድርጋ የምታምን ሀገር ናት ብለዋል።
በዚህ የተሳሳተ እሳቤ ኢትዮጵያንም በንቀት ስትመለከታት እንደኖረች ያነሳሉ። በታሪክ ኢትዮጵያ ከወንዙ በልማት ተጠቃሚ ለመኾን ጥረት ስታደርግም በቀጥታ እና በተዘዋዋሪ ተጽዕኖ ስታደርግባት መቆየቷን ያብራራሉ። ነገር ግን ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን ገንብታ ማጠናቀቋ አስደንግጧቸዋል ነው ያሉት።
ግብጽ በኢትዮጵያ ላይ በጠላትነት መነሳቷ “ውኃው ይቆማል ወይም ይቀንሳል” በሚል እሳቤ ሳይኾን በወንዙ ላይ ከነበራት “የበላይነት ቀረብኝ” አስተሳሰብ የመነጨ መኾኑን ያብራራሉ። በዚህ የተነሳሳችው ግብጽ ኢትዮጵያ በዓባይ ላይ ለመገንባት የወጠነቻቸውን በርካታ የልማት
ፕሮጀክቶች እንዳይሳኩ በተዘዋዋሪ ጥረት ስታደርግ ቆይታለች ነው ያሉት። በውስጥ ጉዳይ በተለያየ መንገድ ጣልቃ በመግባትም እርስ በርስ ለማጋጨት መጣሯን አሁንም ድረስ እንደቀጠለች ያነሳሉ። ከዚህ በፊት ኢትዮጵያ ያልፈረመቻቸው ውሎችን ዋቢ በማድረግ የዓለም ዓቀፍ
ማኅበረሰብን በማሳሳት መሟገትም ሌላው የጠልፎ መጣያ ስልቷ አድርጋለች ነው ያሉት። ይህንን ሁሉ ሴራ እየጠነሰሰች የኖረችው ግብጽ ኢትዮጵያ በዓባይ ላይ የጀመረችው የልማት ፕሮጀክት እንዳስደነገጣት አስረድተዋል። ኢትዮጵያም ታላቁ ሕዳሴ ግድብን እውን በማድረግ በዓባይ
ላይ ተጠቃሚነቷን እና የስኬት ጉዞዋን ማረጋገጥ መጀመሯን ያብራራሉ። በኢትዮጵያ አራት ግድቦችን ለመገንባት ጥናት ተሠርቶ የነበረ ቢኾንም ከአራቱ መካከል ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ አንዱ መኾኑን አንስተዋል። ኢትዮጵያ ያቀደችውን መጀመር አለባት፤ የጀመረችውንም መጨረስ
አለባት ነው ያሉት የታሪክ ተመራማሪው። ታላቁን የሕዳሴ ግድብ ገንብታ እዳጠናቀቀች ሁሉ ቀሪዎቹን ሦስት ግድቦችም መገንባት እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል። ግብጽ ከኢትዮጵያ ጋር በጋራ ተጠቃሚነት መርሕ ተስማምታ መቀጠል እንደሚገባትም ተናግረዋል። ከዚህ በተጻራሪ
መንገድ እና ፍትሐዊ ባልኾነ መንገድ አሁን ላይ በያዘችው አቋም የምትቀጥል ከኾነ እንደማያዋጣት በታሪክም በተደጋጋሚ ታውቀዋለች ነው ያሉት።
✍️ዘጋቢ:- አሰፋ ልጥገበው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleባለዘንባባዋ ከተማ ሹርጉዷን አጠናቅቃ እንግዶቿን እየተቀበለች ነው።
Next articleኢትዮጵያ ከመጀመሪያው ጀምሮ የጣና ፎረምን ዋና ባለቤት ኾና እያስተናገደች ቀጥላለች።