
ኢትዮጵያ በምሥራቅ አፍሪካ ቀንድ የነበራትን ታሪካዊ የባሕር ገዥነት እና የባሕር ኀይል ክብር ዳግም ለማንሳት የጀመረችው ጉዞ ተራ የወታደራዊ ዝግጅት ጉዳይ አይደለም፤ የሕልውና፣ የብሔራዊ ኩራት እና የጂኦ-ፖለቲካዊ ሚዛን የማስጠበቅ ዘመናዊ ራዕይ እንጂ! 🇪🇹✨
📌 የነጭ መለዮ ለባሾቹ ታሪካዊ ትውስታ
የቀደሞው የኢትዮጵያ የባሕር ኀይል በቀይ ባሕር እና በምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና ውስጥ ግርማ ሞገስ ያለው እና የተከበረ የባሕር ኀይል እንደነበረ ታሪክ ይመሰክራል።
ምጽዋ እና አሰብ ላይ የነበሩት የባሕር ኀይል ቤዞች የኢትዮጵያን የንግድ መስመር ከማስጠበቅ ባለፈ የቀጣናውን ሰላም በማስከበር ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደነበራቸው ታሪክ የሚዘክረው ትውልድ የማይረሳው ሀቅ ነው።
በ1980ዎቹ ማጠቃለያ በጂኦ-ፖለቲካዊ ለውጥ ምክንያት የባሕር ኀይሉ ቢበታተንም፣ የሀገራችን ታሪካዊ የባሕር ፍላጎት እና የባሕር ሕልም ግን አልተቋረጠም።
👉የ21ኛው ክፍለ ዘመን ጂኦ-ፖለቲካ እና ዘመናዊው ራዕይ
የኢትዮጵያ የባሕር ኀይል ዳግም መጠናከር ሀገሪቱ ያጣችውን የቀይ ባሕር ስመ-ገናናነት ለመመለስ፣ ብሔራዊ ጥቅም እና የስትራቴጂካዊ ደኅንነትን የማስከበር የወደፊት ረዕይን የሰነቀ ነው።
በመኾኑም ፈርሶ የነበረው ይህ የባሕር ኀይል በአሁኑ ወቅት በሰው ኀይል፣ በትምህርት፣ በተቋማት ግንባታ እና በዓለም አቀፍ ትብብሮች ራሱን በዘመናዊ መልክ እያደራጀ ይገኛል።
130 ሚሊዮን ገደማ ሕዝብ ያላትን ኢትዮጵያ የባሕር ኀይል ዳግም ማጠናከር የምርጫ ሳይኾን የሕልውና ጉዳይ መኾኑን የኢትዮጵያ ባሕር ኀይል ዋና አዛዥ ቫይስ አድሚራል ክንዱ ገዙ ገልጸዋል።
አዛዡ እንደተናገሩት ጠንካራ የባሕር ኀይል ሳይኖር የዚህን ግዙፍ ሕዝብ ሁለንተናዊ ፍላጎት እና ብሔራዊ ጥቅም ማስጠበቅ እጅግ ፈታኝ ነው።
በመኾኑም ተቋሙን ዳግም ማደራጀት እና ማጠናከር ቀጣናዊ እና ሀገራዊ ግዴታ መኾኑን አስገንዝበዋል።
በቀጣናው በሚገኙ ማናቸውም ውኃማ አካላት ላይ ሊቃጡ የሚችሉ ሥጋቶችን ለመከላከል ኢትዮጵያ በቂ ዝግጅት እና አቅም እንዳላት የጠቆሙት ቫይስ አድሚራል ክንዱ ለሀገር ውስጥም ኾነ ለጎረቤት ሀገራት ዘላቂ ደኅንነት ከኢትዮጵያ በላይ አስተማማኝ አጋር ሊኖር እንደማይችል ገልጸዋል።
የባሕር በር ጥያቄን የፍትሐዊነት እና የሕልውና አጀንዳ አድርጎ የተነሳው የዚህ ትውልድ ራዕይ እንዲሳካ ከተቋም ግንባታ ባሻገር ዓለም አቀፍ ዕውቀት እና ልምድ ያላቸውን ብቁ እና ተወዳዳሪ የሰው ኀይል በማፍራት ላይ ይገኛል ነው ያሉት።
ኢትዮጵያ ከ90 በመቶ በላይ ገቢ እና ወጭ ንግዷን በባሕር መስመር የምታከናውን በመኾኗ የባሕር ደኅንነቷን ማስጠበቅ አማራጭ የሌለው ፍላጎቷ ነው፦
የባሕር ላይ ወንበዴነትን እና የደኅንነት ስጋቶችን በመከላከል የሀገሪቱን የንግድ መርከቦች እና የገቢ-ወጭ እቃዎች ዋስትና ያረጋግጣል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በአንድ ወቅት እንደገለጹት “ኢትዮጵያ እያደገ ከሚሄደው የሕዝብ ቁጥሯ፣ ከመሬት ስፋቷ ጋር የሚመጣጠን የደኅንነት ስጋት ለመቋቋም እና የንግድ መስመሮቿን ዋስትና ለመስጠት ጠንካራ እና ዘመናዊ የባሕር ኀይል መገንባት አለባት። ይህን ታሳቢ በማድረግ ኢትዮጵያ የባሕር ኃይሏን እየገነባች ነው።
የባሕር ኀይል መገንባት ለአንድ ሀገር የቅንጦት ሳይኾን የሕልውና እና የጂኦ-ፖለቲካዊ አቅም ማሳያ ስለመኾኑም ጠቁመዋል።
#አሚኮ #የባሕርኃይል #ኢትዮጵያ🇪🇹
#ባሕር_ዳር #መሥከረም _12_2019_ዓ_ም
ዘጋቢ፦ ቴዎድሮስ ደሴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
