“የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የመረዳዳት እና የመተጋገዝ ባሕል እንዲጎለብት አድርጓል” አቶ ይርጋ ሲሳይ

11

 

የአማራ ክልል እና የፌደራል የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ዐቢይ እና የቴክኒክ ኮሚቴ የክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሥራዎችን አፈጻጸምን ገምግሟል።

መርሐ ግብሩ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ይርጋ ሲሳይ የበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ የዜጎችን ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች በከፍተኛ ደረጃ ከመቀነሱም በላይ የመረዳዳት፣ የመተጋገዝ እና የወንድማማችነት ባሕል እንዲጎለብት አድርጓል ብለዋል።

በክልሉ በክረምት ወራት በተከናወነው የተቀናጀ የክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በሁሉም መስኮች አበረታች ውጤት መመዝገቡን ተናግረዋል። ይህ አፈጻጸም በቀጣይ የበጋ ወራት ለሚከናወኑ የሠላም፣ የልማት እና የመልካም አሥተዳድር ሥራዎች አቅም የሚፈጥሩ መኾናቸውን ገልጸዋል።

ከአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የተገኘው መረጃ እንደሚያመላክተው በክረምት ወራት በክልሉ የተከናወኑ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሥራዎች የፓርቲው ሰው ተኮር እሳቤዎች በተግባር የተረጋገጠባቸው ናቸው ብለዋል።

የሴቶች እና የወጣቶች ተሳትፎ በየዓመቱ እያደገ መምጣቱ የማኅበረሰቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ከማረጋገጡም በላይ የእርስ በእርስ ትስስር እና ትብብር እያጠናከረው እንደሚገኝም አንስተዋል።

በመድረኩ የአማራ ክልል ሴቶች፣ ወጣቶች እና ማኀበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኀላፊ ብርቱካን ሲሳይ በክልሉ በበጎ ፈቃድ አገልግሎት የተከናወኑ የአረንጓዴ አሻራ፣ የግብርና ልማት፣ የደም ልገሳ፣ የማዕድ የማጋራት፣ የማጠናከሪያ ትምህርት፣ ለአረጋውያን እና አቅመ ደካሞች አዲስ ቤት ግንባታ እና ነባር ቤት ጥገና እና ሌሎች የተከናወኑ ተግባራትን አቅርበዋል።

#ባሕር_ዳር #መስከረም_12_2019_ዓ_ም

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous article“የኢትዮጵያ የባሕር ኀይል ዳግም ትንሣኤ”
Next articleኢትዮጵያ አትወድቅም፤ የወደቁትን ታነሳለች እንጂ።