
ጠላቶቿ ለዘመናት ሉዓላዊነቷን ሊዳፈሩ፤ ነጻነቷን ሊነፍጉ፤ የታሪክ የበላይነቷን ሊገረስሱ በኅቡህ ተንቀሳቅሰዋል። መንቀሳቀስ ብቻም ሳይኾን ኀያልነቷን ሊነጥቁ ተደጋጋሚ ጥቃት ፈጽመዋል። ኢትዮጵያ ግን ከዓለት በጠነከረ ክንዷ፤ ከነበልባል በሚልቅ ኀይሏ ጠላትን ድባቅ እየመታች ኀያልነቷን አጽንታለች።
👉በኢትዮጵያ የተፈጸሙ የውጭ ጥቃቶች
ኢትዮጵያውያን ዘመኑን የሚመጥን ቴክኖሎጂ ሳይታጠቁ፤ የሥልጣኔ መሠረቶችን ሳይጎናጸፉ፤ ባሕላዊ የጦር መሥሪያ በያዙበት ወቅት ወራሪዎች ኢትዮጵያን ለመውረር ተነሱ።
የሀገር ፍቅርን የተጎናጸፉ፤ የነጻነት ጥቅምን የተረዱ ኢትዮጵያውያን በአንድነት በመቆም በባዶ እግራቸው በየተራራ እና ሸለቆው በመታገል፤ ጠላትን አይቀጡ ቅጣት በመቅጣት ሉዓላዊነታቸውን አስጠብቀዋል። በዓድዋ ድል ከኢትዮጵያ አልፎ ለአፍሪካ ኩራት እና የነጻነት አርማ መኾን ችለዋል።
ጠላቶች በተደጋጋሚ ጥረት ቢያደርጉም ኢትዮጵያ ግን አልተንበረከከችም። ይልቁንም የሀገር ፍቅርን፤ ጀግንነትን፤ አልሸነፍ ባይነትን፤ ለክብር በጽናት መቆምን እና ድል ማድረግን ለዓለም አሳይታለች።
👉የኢትዮጵያ የውስጥ የግጭት ፈተናዎች።
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የግል ፍላጎትን እና የሥልጣን ጥምን ለማርካት ሲባል የውስጥ ግጭቶች ሲካሄዱ ይስተዋላል። ለአብነትም በትግራይ፤ በኦሮሚያ፤ በአማራ እና በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልሎች እና በሌሎች አካባቢዎች የሚንቀሳቀሱ የታጠቁ አካላት የኢትዮጵያ የውስጥ ፈተና ኾነዋል።
ከኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ጎን በመቆም ኢትዮጵያን ለማዳከም ሠርተዋል፤ እየሠሩም ይገኛሉ። ታጣቂዎቹ የንጹሐን ሕይወት እንዲቀጠፍ፤ ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ውድመት እንዲከሰት፤ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ቀውስ እንዲፈጠርም ሠርተዋል።
ኾኖም ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት በውጭ ኀይሎች የሚደገፉ የውስጥ ግጭቶችን በጥበብ አሸንፋለች።
👉የኢትዮጵያ ማሸነፊያ መንገዶች
ለውስጥ ኀይሎች የሰላም አማራጭን በማቅረብ፤ የሰላም አማራጭን በማይቀበሉት ላይ ደግሞ ጠንካራ ሕግ የማስከበር እርምጃዎችን በመውሰድ ፈተናዎችን በድል እየተሻገረች ነው። በጠንካራ ዲፕሎማሲያዊ መንገድ ደግሞ የውጭ ኀይሎችን በማሸነፍ ላይ ትገኛለች።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ኢትዮጵያ መነሳቷን እና እያንሠራራች መኾኗን በተለያዩ ጊዜያት ተናግረዋል። በልጆቿ ደም እና አጥንት በዓድዋ ድል ለአፍሪካ የነጻነት ደወል፤ የነጻነት አርማ መኾኗን ተናግረዋል።
የለመለመች፤ የበለጸገች ሀገርን ለቀጣዩ ትውልድ ለማውረስ እንሠራለን ነው ያሉት። በሁሉም ዘርፎች በጋራ በመሥራት ኢትዮጵያን እናሻግራለን ብለዋል። ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት ዘርፈ ብዙ ፈተናዎችን በድል ማለፏንም ገልጸዋል።
ሰላምን በማጽናት፤ በኅብረት እና በጋራ በመቆም ኢትዮጵያን ማሳደግ ይገባል ብለዋል። ባለፉት ዘመናት ችግሮችን በኀይል ለመፍታት መሞከር፤ የባንዳነት አመል እና ጠላቶች የኢትዮጵያን ዕድገት መፍራት የኢትዮጵያ ፈተና እንደነበር ተናግረዋል።
የኢትዮጵያን ልዕልና በሚገዳደር ጉዳይ ላይ በጋራ መቆም የፖለቲካ ስብዕናን አያሳጣም ነው ያሉት። የኢትዮጵያን የሰላም መደፍረስ ምንጩን ስለምናውቅ ከምንጩ የሚነሳን ማንኛውንም ትንኮሳ ለመከላከል የሚያስችል ቁመና በመፍጠር ላይ እንገኛለንም ብለዋል።
“ኢትዮጵያ አትወድቅም የወደቁትን ታነሳለች፣ የተኙትን ታነቃለች” ነው ያሉት።
#ፈተናዎችን_መሻገር #ኢትዮጵያ🇪🇹 #አሚኮ
#ባሕር_ዳር #መሥከረም _12_2019_ዓ_ም
ዘጋቢ:- ያየህ ፈንቴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
