
ባሕር ዳር: ግንቦት 27/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ወቅቱን መገንዘብ እና ተገቢውን ቅድመ ጥንቃቄ ማድረግ እጅግ መሠረታዊ ነገር ነው።
ሞቃታማው ወራት አልፎ ቅዝቃዜ ከሚተካበት ወራት ልንደርስ ጫፍ ላይ እንገኛለን። ይህ ወቅት ታዲያ ጥንቃቄ የሚፈልግ ጊዜ ነው።
በተለይም ለሰው ልጅ የጤና ጠንቅ የኾነችው ወባ አምራቹን በስፋት ልታጠቃ የምትችልበት ምቹ አጋጣሚ የሚፈጠርበትም ጊዜ ነው። በባሕር ዳር ከተማ አንዳንድ አካባቢዎች ዜጎች በወባ ተጠቅተው በጤና ጣቢያዎች መገኘት ጀምረዋል።
በባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ጤና መምሪያ የኅብረተሰብ ጤና አደጋዎች መከላከያ እና መቆጣጠሪያ አሥተባባሪ ይዘንጋው መኮንን በክረምት መግቢያ እና መውጫ ላይ ያሉ ጊዜያቶችን ሰዎች ጥንቃቄ ማድረግ ካልቻሉ በወባ መጠቃታቸው አይቀሬ ይኾናል ይላሉ።
አሁን ላይ በከተማው በወባ የመጠቃት ሁኔታ በየሳምነቱ እየጨመረ መሄዱን ከጤና ጣቢያዎች የሚደርሰው መረጃ እየጠቆመ እንደሚገኝም ተናግረዋል።
ከተማ አሥተዳደሩ ቀድሞ ወባን ለመከላከል ቅድሚያ ተጠቂ ናቸው ላላቸው እና አቅማቸው አነስተኛ ለኾኑ 26 ሺህ ዜጎች አጎበር ማሰራጨቱን ጠቁመው ሰዎች በተገቢ መንገድ እንዲጠቀሙበትም አስገንዝበዋል።
አጎበር ያላገኙ የከተማዋ ነዋሪዎችም ለበሽታው ትኩረት በመስጠት ከዚህ በፊት የተሠራጨውን በሚገባ ጥቅም ላይ የማዋል እና መግዛት የሚችሉ ደግሞ ገዝተው በመጠቀም ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ነው አስተባባሪው የመከሩት።
ከተማ አሥተዳደሩ የዜጎችን ጤና መጠበቅ ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር ነው የሚሉት አሥተባባሪው የአርብ ጠንካራ እጆች በሚል የጽዳት ዘመቻ ሲያካሂድ መቆየቱን ገልጸዋል። ኅብረተሰቡ ከጥቅሙ አንጻር ተረድቶ በሚገባው ልክ እየተረባረበ ባለመኾኑ እንዲሳተፍ ነው ያስገነዘቡት።
ወባን ለመከላከል ዋነኛው ሥራ የአካባቢ ጽዳት እንደኾነ ጠቁመው ለሥራው ትኩረት እንዲሰጥም ነው ያስረዱት።
በባሕር ዳር ከተማ አሁን ላይ በወባ የመጠቃት አዝማሚያ እያሳዩ ያሉት ቀበሌ 11 (ዓባይ ማዶ)፣ መሸንቲ እና በላይ ዘለቀ ክፍለ ከተማ መኾናቸውን ለአብነት አንስተዋል። ለጊዜው እነዚህ አካባቢዎች ይበልጥ ትኩረት እንደሚሹ ነው ያብራሩት።
ሌሎች አካባቢዎችም ወቅቱ ለወባ ምቹ የኾነ ጊዜ መኾኑን በመረዳት ጥንቃቄ ማድረግ ይገባቸዋል ነው ያሉት።
በከተማዋ 10 ጤና ጣቢያዎች፣ 11 ጤና ኬላዎች፣ እና 3 ሆስፒታሎች ኅብረተሰቡን እያገለገሉ ስለመኾኑ የጠቆሙት አስተባባሪው ተቋሞቹ ለወባ ለካርድ ክፍያ ካልኾነ በስተቀር መድኃኒት በነጻ በመኾኑ ትኩሳት ሲኖር በፍጥነት ወደ ሕክምና መሄድ ይገባል ነው ያሉት። በጤና ተቋሞቹም በቂ የኾነ መድኃኒት ስለመኖሩም ነው ያስረዱት።
አምራች እና ለሀገር ወሳኝ የኾነው ኃይል በወባ እንዳይጎዳ ግን ጥንቃቄ ማድረግ እና ግንዛቤ መፍጠር እንደሚገባም ነው የጠቆሙት።
በምሥጋናው ብርሃኔ
የአሚኮ ዲጂታል ቤተሰብ ይሁኑ !
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
