☘️🌿በአማራ ክልል ከ1 ነጥብ 7 ቢሊዮን በላይ ችግኝ ለአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ተዘጋጅቷል።

16

 

ባሕር ዳር: ግንቦት 26/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር እንደ ሀገር ሰፊ ትኩረት ተሰጥቷቸው ከሚከናወኑ ተግባራት መካከል አንዱ ነው። መርሐ ግብሩ የደን ሽፋንን ከማሳደግ እና የአፈርን መሸርሸር ከመከላከል ባለፈ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል ድርሻው የጎላ ነው።

የደቡብ ጎንደር ዞን ግብርና መምሪያም የደን ሽፋንን ከፍ ለማድረግ እና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸውን ችግኞች ለተከላ ለማዘጋጀት አቅዶ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እየሠራ መኾኑን የመምሪያው ምክትል ኀላፊ አባተ ሽባባው ገልጸዋል። በችግኝ ተከላ ወቅትም ከማህበረሰቡ ጋር በቅንጅት እንደሚሠራም ተናግረዋል።

🗺️ በዞኑ 28 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ለችግኝ ለተከላ የማዘጋጀት ሥራም ተሠርቷል።

🌱 ለተከላ ከታቀደው 213 ሚሊዮን የደን፣ የእንስሳት መኖ እና ሌሎችም ችግኞች መካከል 90 በመቶው የሚኾነው ተዘጋጅቷል።

🍅🥭 ለአርሶ አደሮች ቀጥተኛ ጥቅም የሚውሉ የቡና እና የፍራፍሬ (ፓፓያ እና ማንጎ) ችግኞችን ለመትከል የማዘጋጀት ሥራም እየተሠራ ይገኛል።

🌱☘️ አርሶ አደሮች በተፋሰስ ልማት እንዲደራጁ እና ባለቤት እንዲኾኑ የማድረግ ሥራም ይሠራል ነው ያሉት።

ባለፉት ዓመታት የተተከሉ ችግኞችን ማኅበረሰቡ በባለቤትነት እንዲንከባከብ በመደረጉ የችግኞቹ የጽድቀት ደረጃ ከፍ ብሏል ነው ያሉት። በዚህም ማኅበረሰቡ ተጠቃሚ እየኾነ መኾኑን ነግረውናል።

አቶ አባተ እንደተናገሩት በዞኑ አሁን ካለው የደን ሽፋን 14 ነጥብ 7 በመቶ ወደ 15 ነጥብ 7 በመቶ ለማሳደግ ታልሞ እየተሠራ ነውም ብለዋል።

​በቀጣይም ችግኞችን ወደ መትከያ ቦታ የማጓጓዝ እና ማኅበረሰቡን በንቅናቄ በማሳተፍ እያንዳንዱ ዜጋ የአረንጓዴ አሻራ ሥራ ላይ የድርሻውን እንዲወጣ የማድረግ ሥራዎች በትኩረት እንደሚሠሩም ተገልጿል።

የዘንድሮውን 8ኛ ዓመት የሁለተኛው ምዕራፍ ማጠናቀቂያ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ስኬታማ ለማድረግ ሰፊ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እየተከናወኑ መኾኑን የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ አስታውቋል። የቢሮው ኀላፊ ደረጀ ማንደፍሮ እንደገለጹት፤ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸውን፦
🌱 1 ነጥብ 78 ቢሊዮን ችግኞች ለማዘጋጀት ታቅዷል
🌱 እስካሁን 1 ነጥብ 72 ቢሊዮን (97 ነጥብ 3 በመቶ) ችግኞች ተዘጋጅተዋል
🌱ከ261 ሺህ ሄክታር በላይ የተከላ ቦታ ተለይቶ የችግኝ መትከያ ጉድጓድ ዝግጅት ሥራ በቅንጅት እየተከናወነ ይገኛል ነው ያሉት።

የአረንጓዴ አሻራ ኢኒሼቲቭ በሀገሪቱ ሁለንተናዊ ዕድገት እና በኅብረተሰቡ የሥራ ባሕል ላይ ከፍተኛ ለውጥ ማምጣቱን ኀላፊው ገልጸዋል። ማኅበረሰቡ የሥራው ዋና ባለቤት በመኾን ጉልበቱን፣ ዕውቀቱን እና ጊዜውን በመስጠት ባደረገው ጥበቃ እና እንክብካቤ ምክንያት ቀደም ሲል የተተከሉ ችግኞች የመጽደቅ መጠን በእጅጉ ከፍ ሊል መቻሉን አቶ ደረጀ አብራርተዋል።

ይህ ሀገራዊ ንቅናቄ የአካባቢን ሥነ-ምህዳር ለመጠበቅ እና የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን ለመከላከል ትልቅ አቅም ከመኾኑም በላይ ሁሉንም ኢትዮጵያውያን በአንድነት ያስተሳሰረ የልማት ሥራ ነው ብለዋል። ዛሬ የሚተከሉ ችግኞች የነገው ትውልድ እስትንፋስ እና ለምለም ሀገርን ለማሸጋገር ዋስትና በመኾናቸው ለዚሁ ስኬት በየደረጃው ያሉ የዝግጅት ተግባራት በቁርጠኝነት ሊሠሩ እንደሚገባ ተነግሯል።

#አሚኮ_ዜና #የችግኝ_ዝግጅት #አማራ_ክልል #ኢትዮጽያ

ዘጋቢ ፦ሥራውድንቅ ደሳለው

የአሚኮ ዲጂታል ቤተሰብ ይሁኑ !

https://linktr.ee/Amharamediacorporations

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !

Previous article“7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ወጣቶች ፖለቲካዊ ተሳትፎ እና ሀገራዊ ኀላፊነታቸውን የተወጡበት ነበር” የኢትዮጵያ ወጣቶች ፌዴሬሽን
Next articleየክረምቱን መግባት ተከትሎ ከሚከሰት የወባ በሽታ ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል።