ኢትዮጵያ የቱሪዝም ባለጸጋ ናት

4
🇪🇹
#ባሕር_ዳር: ሰኔ 26/2018 ዓ.ም ኢትዮጵያ በተፈጥሮ፣ በታሪክ፣ በባሕል እና በሃይማኖታዊ እሴቶች የበለጸጉ በርካታ የቱሪዝም ሀብቶች ያሏት ሀገር ናት። የኢትዮጵያ የቱሪዝም ሀብት ከታሪክ ተመራማሪዎች እስከ ተፈጥሮ አድናቂዎች፣ ከሃይማኖት ተጓዦች እስከ ባሕል አጥኝዎች ለሁሉም የሚኾን ሰፊ አማራጮችን ያካተተ ነው።🗺️
ከደጋ እስከ ቆላ የሚያካልል ሥነ ምኅዳር፣ ከከፍተኛ ሙቀት እስከ ቅዝቃዜ የሚደርስ የአየር ንብረት እና ከራስ ደጀን እስከ ዳሎል የሚዘልቅ ውብ መልከዓምድር የሀገሪቱን የብዝኀ ቱሪዝም ጸጋን በግልጽ ያሳያል።
የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት፣ የሀረር ጀጎል ግንብ፣ የጎንደር አብያተ መንግሥታት፣ የአክሱም ሐውልት፣ የሶፍ ዑመር ዋሻዎች እና ሌሎች በርካታ አስደናቂ የባሕል እና የታሪክ ሀብቶችም በኢትዮጵያ የቱሪዝሙ መሠረት ናቸው።🏰
በተጨማሪም ከ6ሺህ በላይ ለሚኾኑ የዕፅዋት ዝርያዎች፣ እንደ ዋሊያ አይቤክስ፣ ጭላዳ ዝንጀሮ እና ቀይ ቀበሮ ያሉ ብርቅየ እንስሳትም ባለቤት ናት።🌿
እነዚህ ተፈጥሯዊ እና ባሕላዊ ጸጋዎች ተደምረው ኢትዮጵያን ዘርፈ ብዙ የቱሪስት መዳረሻ እና በቱሪዝም ዘርፍ ሀብታም እንድትኾን አስችሏታል።🌳🦅
ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት ለቱሪዝም ዘርፉ ትልቅ ትኩረት ሰጥታለች።
ሀገሪቱ ባላት የቱሪዝም ጸጋ፣ በዓለም አቀፋዊ ተወዳዳሪነት እና ዘርፉ ሊያመጣ የሚችለውን የኢኮኖሚ ተፅዕኖ በውል በመረዳት ቱሪዝም አንዱ የልማት ምሰሶ ተደርጎ እየተሠራበት ነው።
🎯መንግሥት ከአሥር ዓመቱ የልማት ዕቅድ ጋር በማስተሳሰር ጸጋዎቿን ወደ ኢኮኖሚ ለመቀየር የሚያስችሉ የፖሊሲ ለውጥ አድርጓል። ሀገሪቱን ተወዳዳሪ እና አስተማማኝ የቱሪስት መዳረሻ የማድረግ ራዕይም ተሰንቋል።
ይህንን ለማሳካት በተደረገው ለውጥ አሁን ላይ የሚጨበጡ ውጤቶች ተመዝግበዋል። ባለፉት ጥቂት ዓመታት ብቻ ሰባት አዳዲስ የአውሮፕላን ማረፊያዎች ተጠናቅቀው ለአገልግሎት ክፍት ኾነዋል።✈️
በገበታ ለሀገር፣ በገበታ ለትውልድ እና በመሰል መርሐ ግብሮች አማካኝነት በሀገር አቀፍ ደረጃ አዳዲስ የቱሪስት መዳረሻዎች ተገንብተዋል። ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ የሥብሠባ ማዕከላት፣ መንገዶች እና የዲጂታል መሠረተ ልማት ሥርዓቶች ተዘርግተዋል።🌐🛣️
ለቱሪዝም መሠረት የኾኑ እና ተጎድተው የነበሩ በርካታ ታሪካዊ ቅርሶች ተጠግነው ለጉብኝት ክፍት ኾነዋል። ከ35 በላይ ቅርሶችም ወደ ኢትዮጵያ እንዲመለሱ ተደርጓል።
በተሠራው ሥራም ተስፋ ሰጭ ውጤቶች ተመዝግበዋል። ለአብነትም በበጀት ዓመቱ ከ1 ነጥብ 4 ሚሊዮን በላይ የዓለም አቀፍ ጎብኝዎች ሀገሪቱን ጎብኝተዋታል። ከዚህም 5 ነጥብ 2 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ተገኝቷል።
በተመሳሳይ ከ50 ሚሊዮን በላይ ኢትዮጵያውያን በሀገር ውስጥ ያሉ ቦታዎችን ጎብኝተዋል። ይህም ካለፈው ዓመት በ1 ነጥብ 8 ሚሊዮን ጭማሪ ያሳየ ነው። ከ79 ቢሊዮን ብር በላይም ገቢ አስገኝቷል።
በኮንፈረንስ ቱሪዝምም አዲስ ስኬቶችን እያስመዘገበች ትገኛለች። በበጀት ዓመቱ ኢትዮጵያ 204 የዓለም አቀፍ ጉባኤዎችን በስኬት ማስተናገድ ችላለች። ይህም ካለፉት ሁለት ዓመታት በ166 ብልጫ አሳይቷል።
ባለፉት ዓመታት የቱሪዝም ጸጋዎችን በማስተሳሰር ወደ ሁለንተናዊ የኢኮኖሚ ዕድገት ለመለወጥ በተሠራው ሥራ ተጨባጭ ውጤት መምጣቱን ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመላክታል።
ዘጋቢ:- አሰፋ ልጥገበው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ( ዶ.ር) የዶርዜ ሎጅ የቱሪዝም መዳረሻን ጎበኙ።