ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ( ዶ.ር) የዶርዜ ሎጅ የቱሪዝም መዳረሻን ጎበኙ።

6
#ባሕር_ዳር: ሰኔ 26/2018 ዓ.ም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ( ዶ.ር) የዶርዜ ሎጅ የቱሪዝም መዳረሻን ጎብኝተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት የጫኖ-ጨንቻ መንገድ ፕሮጀክት የደረሰበትን ፈጣን የግንባታ ሂደት ዛሬ ተመልክተናል ብለዋል።
የ22 ኪሎ ሜትር የጫኖ ጨንቻ መንገድ እና የሰባት ኪሎ ሜትር የኤዞ-ጊርጫ ቅርንጫፍ መንገድን የያዘው የ29 ኪሎ ሜትር ፕሮጀክት በጥሩ አፈጻጸም ላይ ነው። 13 ነጥብ 3 ኪሎ ሜትር ሥራው ተጠናቅቋል። የመንገዱ ሥራ ‎ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቅ የማኅበረሰቡን ትስስር ይበልጥ ያጠናክራል፣ ንግድ እና ጉዞን ያቀላጥፋል፣ የአካባቢውን የኢኮኖሚ ልማት ያፋጥናል ነው ያሉት።
‎በዚሁ ጉብኝታችን ከ1997 ዓ.ም ጀምሮ በማኅበረሰቡ ጠንካራ መሪነት የያዘው እና የታደሰውን የዶርዜ ሎጅ የቱሪዝም መዳረሻ መጎብኘታቸውን ገልጸዋል። በ40 ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ፣ በቀዝቃዛው እና ሰንሰለታማ የተራራ ጋራ ላይ ያረፈው ይህ አስደናቂ ሥፍራ፣ የአባያና ጫሞ ሐይቆችን፣ “የእግዜር ድልድይ” ተብሎ የሚጠራውን የተፈጥሮ ድንቅ ዕይታ በአንድ ላይ በግልጽ የሚያሳይ ውብ ገጽታን ይሰጣል ብለዋል።
‎እንደ ዶርዜ ሎጅ ያሉ መሰል የቱሪስት መዳረሻዎች ጎን ለጎን የሚከናወነው የመንገድ መሠረተ-ልማት መስፋፋት፣ ስፍራው ያለውን እጅግ ከፍተኛ የኢኮኖሚ እና የባሕል አቅም ሙሉ በሙሉ አውጥቶ ለመጠቀም በእጅጉ ያግዛል። በሃገር ውስጥ እና በውጭ ሃገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን፣ የዲያስፖራ አባላት እና ከመላው ዓለም የሚመጡ ጎብኚዎች ይህንን አስደናቂ የተፈጥሮ ውበትና የበለጸገ የባሕል ሐብት እንዲጎበኙ እና የታሪኩ ተጋሪ እንዲኾኑ ጥሪ አቅርበዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous article“የላቀ የፍትሕ አገልግሎት፣ ተደራሽነት እና የሰብዓዊ መብት ጥበቃ ዋነኛ የትኩረት ማዕከል ናቸው” አቶ ዓለምአንተ አግደው