“የላቀ የፍትሕ አገልግሎት፣ ተደራሽነት እና የሰብዓዊ መብት ጥበቃ ዋነኛ የትኩረት ማዕከል ናቸው” አቶ ዓለምአንተ አግደው

3
⚖️
#ባሕር_ዳር: ሰኔ 26/2018 ዓ.ም የአማራ ክልል የዳኝነት እና የፍትሕ አካላት የትብብር መድረክ የ2018 በጀት ዓመት አፈጻጸሙን እየገመገመ ነው።
የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት እና የዳኝነት እና የፍትሕ አካላት የትብብር መድረክ ሠብሣቢ ዓለምአንተ አግደው የፍትሕ ዘርፍ ሥራዎች አንዱ ለሌላው ግብዓት በመኾናቸው መድረኩ በፍትሕ ተቋማት መካከል የተቀናጀ አሠራርን ለመፍጠር ወሳኝ መኾኑን ተናግረዋል።
የፍትሕ ዘርፉ ለሀገሪቱ የኢኮኖሚ፣ ማኅበራዊ እና ዴሞክራሲያዊ ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው። ሰላምና የሕግ የበላይነት የተረጋገጠበት፣ ተደራሽና የሕዝብ አመኔታ ያተረፈ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃም ተጠቃሽ የኾነ የዳኝነትና የፍትሕ ሥርዓት ለመፍጠር መታቀዱን ጠቁመዋል። የሕግ የበላይነት፣ የዳኝነት ነጻነት፣ የላቀ የፍትሕ አገልግሎት፣ ተደራሽነት እና የሰብዓዊ መብት ጥበቃ ዋነኛ የትኩረት ማዕከል ተደርገው እየተሠራባቸው ነው ብለዋል።
በዓመቱ ስኬታማ ሥራዎች መሠራታቸውን ያነሱት ፕሬዝዳንቱ በሰው ሀብት ልማት የሕግና ፍትሕ ኢንስቲትዩት የብቃት ማዕከል እንዲኾን ተቋማዊ ሪፎርም ተደርጎለታል። የፖሊስ ኮሌጅም ወደ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ እንዲያድግ ተደርጎ ለመሪዎችና ባለሙያዎች በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር ሥልጠናዎች መሰጠቱን ተናግረዋል።
ተገልጋዩን ከወጭና እንግልት ለመታደግ የዲጂታላይዜሽን ሥራ በስፋት ተሠርቷል። ስማርት ችሎት፣ ኢ-ፋይሊንግ፣ የሰነዶች ምዝገባና ማረጋገጫ፣ የወንጀል ጥቆማና ምርመራ ሥራዎች በቴክኖሎጂ ታግዘው ተግባራዊ ተደርገዋል ነው የተባለው።
የፍትሕ ተደራሽነትን ይበልጥ ለማስፋትም የባሕል ፍርድ ቤቶች ተደራጅተው ወደ ሥራ ገብተዋል። ከእርቅና ከግልግል ዳኝነት ጋር በተያያዘም መልካም ጅማሮዎች ታይተዋል። የጠበቆች ማኅበር ወደ ሥራ እንዲገባ መደረጉና የተከላካይ ጠበቆችን አሠራር ለማሻሻል የተሠሩ ሥራዎችም በበጎ ተነስተዋል።
የአሥተዳደር ፍትሕ ውጤታማነትን ለመጨመር አዳዲስ የሕግ ማዕቀፎች ወጥተው እየተተገበሩ ነው። ፍርድ ቤቶች ልዩ ችሎቶችን በማቋቋም ሕጉን በአጭር ጊዜ ውስጥ ተግባራዊ ለማድረግ ጥረት አድርገዋል ብለዋል።
የተቀናጀ የወንጀል መከላከል ስትራቴጂ ከፖሊስና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በጋራ መዘጋጀቱም ተገልጿል። የአማራ ክልል የዳኝነት እና የፍትሕ አካላት መረጃ ማዕከል መቋቋሙ፣ የመረጃ አሥተዳደር መመሪያ ጸድቆ ወደ ሥራ መግባቱ፣ በአዲሱ በጀት ዓመት ወደ ሥራ የሚገባ የዳታ መጋራት ስምምነትም በስኬት ተነስተዋል።
በኤግዚቢት አያያዝና ከወንጀል የሚገኝ ገንዘብ አሠባሠብ ላይ ጠንካራ የትብብር ሥርዓት መዘርጋቱንም ጠቁመዋል። እነዚህ ውጤቶች የተመዘገቡት በከፍተኛ የሥራ ተነሳሽነት በመኾኑ በቀጣይም አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ አሳስበዋል።
ዘጋቢ፦ስማቸው አጥናፍ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleየከተሞች ልማታዊ ሴፍቲኔት ድህነትን እየቀነሰ ነው።
Next articleጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ( ዶ.ር) የዶርዜ ሎጅ የቱሪዝም መዳረሻን ጎበኙ።