የከተሞች ልማታዊ ሴፍቲኔት ድህነትን እየቀነሰ ነው።

3
#ባሕር_ዳር: ሰኔ 26/2018 ዓ.ም የአማራ ክልል ከተማ እና መሠረተ ልማት ቢሮ የከተሞች ልማታዊ ሴፍቲኔት ሥራ ፕሮጀክት የ2018 በጀት ዓመት አፈጻጸሙን ገምግሟል።
የአማራ ክልል ከተማ እና መሠረተ ልማት ቢሮ ኀላፊ ሞላ መልካሙ (ዶ.ር) የከተማ ምግብ ዋስትና እና የሴፍቲኔት መርሐ ግብር መንግሥት ትኩረት ከሰጣቸው ተግባራት መካከል ወሳኞቹ መኾናቸውን ተናግረዋል።
በፕሮግራሙ አምስት ፕሮጀክቶች እንደሚገኙ አንስተዋል። እነዚህም የልማታዊ ሴፍቲኔት፣ የወጣቶች ብቃት ማረጋገጫ ሥልጠና፣ የቀጥታ እርዳታ፣ የተቋማት ግንባታ እና የአደጋ ጊዜ አስቸኳይ ምላሽ ሰጭ ፕሮጀክት መኾናቸውን ጠቅሰዋል።
በክልሉ የሴፍቲኔት መርሐ ግብር በአንድ ከተማ ተጀምሮ አሁን በ18 ከተሞች እየተተገበረ ነው ብለዋል። በፕሮጀክቶቹ በክልሉ ከ606 ሺህ በላይ የኅብረተሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ መኾናቸውንም ተናግረዋል።
ልማታዊ ሴፍቲኔት በክልሉ መሥራት እየቻሉ ዕድል አጥተው ከቤታቸው የተቀመጡ እና ወደ ከፋ ድህነት ሊገቡ የሚችሉ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ታድጓል ነው ያሉት። በተጨማሪም በተለያዩ ከተሞች የማኅበራዊ አገልግሎት መስጫ ተቋማት እንዲገነቡና በርካታ ወጣቶች የሥራ ዕድል ተጠቃሚ እንዲኾኑ አድርጓል ብለዋል።
በከተሞች ያለውን ድህነት በመቀነስ ትልቅ አስተዋጽኦ በማድረግ ሀገር እና ሕዝብ እየታደገ የሚገኝ ትልቅ መርሐግብር መኾኑንም ገልጸዋል።
የፌዴራል መንግሥት ለመርሐግብሩ ከፍተኛ ትኩረት መስጠቱን ያነሱት ኀላፊው በ2018 በጀት ዓመት ብቻ በሀገር አቀፍ ደረጃ 15 ቢሊዮን ብር እንደበጀተለት አንስተዋል።
መርሐግብሩ ሰው ተኮር ነው ብለዋል። ሰዎችን ከተረጅነት በማላቀቅ ወደ አምራችነት የማሸጋገር ዓላማ አድርጎ የሚንቀሳቀስ ነውም ብለዋል።
መርሐግብሩ ባለባቸውም ኾነ በሌለባቸው ከተሞች የማኅበረሰቡን የምግብ ዋስትና የማረጋገጥ እና ከተረጅነት ወደ አምራችነት የማሸጋገር ሥራ መሥራት እንደሚገባ አመላክተዋል።
ዘጋቢ፦ አድኖ ማርቆስ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleዘምዘም ባንክ የሰነድ መዋዕለ ንዋይ ምዝገባ ማረጋገጫ አገኘ።
Next article“የላቀ የፍትሕ አገልግሎት፣ ተደራሽነት እና የሰብዓዊ መብት ጥበቃ ዋነኛ የትኩረት ማዕከል ናቸው” አቶ ዓለምአንተ አግደው