
ባሕር ዳር፡ ሚያዝያ 18/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ስሟን መግለጽ ያልፈለገች አንዲት ወጣት ከሁለት ዓመት በፊት በባሕር ዳር ከተማ በአልባሳት ንግድ ሥራ ዘርፍ ተሠማርታ ስትሠራ እንደነበር ለአሚኮ ዲጂታል ተናግራለች።
በወቅቱ ቤተሰቦቿ ከሰጧት የሥራ መንቀሳቀሻ ገንዘብ ውስጥ 60 ሺህ የሚኾነውን ቀንሳ ለምትከራየው ቤት የቁልፍ ክፍያ መክፈሏን አጫወተችን።
ያለ ቁልፍ ክፍያ የንግድ ቤት መከራየት አይታሰብም ነው ያለችን። ይህ የኾነው ደግሞ አማራጭ በማጣት በእርሷ እና ቀድሞ ቤቱን ተከራይቶ በነበረ ተከራይ ድርድር እንደነበር አስታውሳለች።
ወጣቷ ወደፊቷን በብዙ ብታስብም በንግድ ሥርዓቱ መቀጠል እንዳልቻለች ነው ያጫወተችን። አሁን ላይ በአንድ የግል ተቋም ተቀጥራ እየሠራች እንደምትገኝም ገልጻልናለች።
ከጉዳዩ ጋር ተያይዞ አሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ያነጋገራቸው የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ደንብ ማስከበር መምሪያ ኀላፊ ኃይለሚካኤል አርዓያ ወደ ንግድ ሥርዓቱ የሚገቡ ግለሰቦች የንግድ ቤቶችን ለመከራየት የሚከፍሉት የቁልፍ ክፍያ መነሻው ሕገ ወጥነት መኾኑን ነግረውናል።
ከተማ አሥተዳደሩ ቀደም ሲል ሕጋዊ መሠረት ከሌለው የንግድ ቤት ኪራይ ቁልፍ ክፍያ አኳያ ብዙ እንዳልሠራ ተናግረዋል። በተጨባጭ ማስረጃ ጥቆማ እንዳልተሰጣቸውም ጠቅሰዋል። በቀጣይ እንዲህ ዓይነት ደንብ መተላለፎች እና ሕገ ወጥነቶች ሲኖሩ ማኅበረሰቡ ለመምሪያው እንዲያሳውቅ ጠይቀዋል።
የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን የሕግ ባለሙያ ፍቅር በለጠ ሕገ ወጥ የንግድ ቤቶች የቁልፍ ክፍያ የሚጠይቁ ሰዎች ከሕግ የሚመነጩ ኀላፊነቶች መካከል አንዱ በኾነው በፍትሐብሔር ኀላፊነት ተጠያቂ እንደሚኾኑ ነግረውናል።
ፍትሐብሔራዊ ኀላፊነት ውልን መሠረት አድርጎ የሚኖር ኀላፊነት እና ከውል ውጪ በሚኖር ግንኙነት የሚፈጠር ኀላፊነት በሚል በሁለት ተከፍሎ ሊታይ እንደሚችልም አስረድተዋል።
ከውል ውጪ ኀላፊነት ውልን መሠረት ያላደረገ ፍትሐብሔራዊ ተጠያቂነትን የሚያመጣ እና ኀላፊነታቸውን ያልተወጡ (የጣሱ) ሰዎች በካሳ መልክ ሊከፍሉት የሚገባ ግዴታ ነው ብለዋል። ሕገ ወጥ የንግድ ቤቶች የቁልፍ ክፍያም በዚህ መሠረት እንደሚያስጠይቅ አስገንዝበዋል።
ከውል ውጭ በኾነ ኀላፊነት አንድን ሰው ተጠያቂ ለማድረግ ግን ድርጊት፣ ግድፈት፣ ጉዳት፣ የምክንያት እና የውጤት ግንኙነት እና የደረሰው ጉዳት በሕግ እውቅና የተሰጠው መኾንን የሚያስፈልጉ ቅድመ ሁኔታዎች እንደኾኑ ነው የተናገሩት።
በሌላ ሰው የሥራ ድካም ወይም የሌላ ሰው ሃብት በኾነ ነገር በመገልገል በቂ ባልኾነ ምክንያት ጥቅም ያገኘ ሰው ያለአግባብ ጥቅም ባገኘበት መጠን እና ለባለ ሃብቱ ወይም ጉልበቱ ለደከመው ሰው ይህ አድራጎት በደረሰበት ጉዳት መጠን ኪሳራውን መክፈል እንዳለበትም የፍትሐብሔር ሕጉ አንቀፅ 2161 ይገልጻል ብለዋል።
ሊከፈል የማይገባን ነገር የከፈለ ሰው እንዲመለስለት በሕግ የመጠየቅ መብት አለውም ነው ያሉት።
ከዚህ በተጨማሪ የተከፈለውን ነገር ከከፈለበት ቀን ጀምሮ የሰጠውን ፍሬ ወይም ሕጋዊውን ወለድ ጭምር እንዲመልስለት መጠየቅም ይችላል ብለዋል።
ቀድሞ ከአከራይ በውል የተከራየው ተከራይ በውል ስምምነታቸው ላይ ካልተገለጸ በስተቀር ተከራዩ እራሱ የተከራየውን ንብረት በሙሉ ወይም በከፊል ማከራየት እንደሚችል የፍትሐብሔር ሕግ አንቀፅ 2957 ቢፈቅድም ቀድሞ ለአከራዩ የማሳወቅ እና አከራዩ መፍቀዱን በግልጽ ማወቅ እንደሚገባው ተቀምጧል ብለዋል። ይህ ሳይኾን ለሌላ ሰው በማከራየት ያልተገባ ጥቅም ማግኘት እንደማይቻልም አንስተዋል።
ከዚህ ባሻገር ሕገ ወጥ የንግድ ቤቶች የቁልፍ ክፍያ በሌሎች ሕጎችም ተጠያቂ ሊያደርግ እንደሚችልም ጠቁመዋል።
ስለዚህ “የቁልፍ ክፍያ” ሠርተው መለወጥ የሚፈልጉ ግለሰቦችን የሚበዘብዝ እና ጀማሪ ነጋዴዎችን በእጅጉ ስለሚጎዳ መቆም ያለበት ተግባር ነው። እንዲህ አይነት ከሕግና አሠራር ያፈነገጡ ሰዎች ሲገጥሙም ማኅበረሰቡ በመጠቆም እና ወደሕግ በማቅረቡ በጋራ ሊሠራ ይገባል።
ዘጋቢ፦ ሮዛ የሻነህ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/Amharamediacorporations
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
