
በምስራቅ ጎጃም ዞን ሰላምን ሲያውክ የቆየው ፅንፈኛ ቡድን እየተወሰደበት ባለው እርምጃ እየተዳከመ፣ እየተመናመነና ወደ ተራ ሽፍትነት እየወረደ ነው ሲሉ የ6ኛ ዕዝ ዋና አዛዥ ሜጀር ጀኔራል ብርሃኑ ጥላሁን ገልጸዋል።
ሜጀር ጀኔራል ብርሃኑ ጥላሁን ከሠራዊቱ ከፍተኛ አመራሮች፣ ከፀጥታ አካላት፣ ከዞንና ከወረዳ የሥራ ኃላፊዎች ጋር በዞኑ አሁናዊ የሰላምና የፀጥታጉዳይ ዙሪያ በደብረ ማርቆስ ከተማ ተወያይተው የቀጣይ የሥራ አቅጣጫ አስቀምጠዋል።
ዋና አዛዡ የምስራቅ ጎጃም ዞን ከነበረበት አስከፊ የሰላም እጦት ተላቆ አሁን ወደ ሚገኝበት አዲስ የሰላምና የሥልጣኔ ምዕራፍ እንዲሸጋገር በየ ደረጃው ያሉ አመራሮች ሚና የጎላ እንደነበር አንስተዋል።
ሜጀር ጀኔራል ብርሃኑ ጥላሁን በተለይም ሰሞኑን የፅንፈኛ ቡድኑ ዋና ቋጠሮ በመሆን የሚታወቀውና እንደ ዋና ይዞታና ሎጀስቲካዊ ማከማቻነት ሲጠቀምበት የነበረው የጮቄ አካባቢ መመታቱን ተከትሎ ከፍተኛ የሆነ ሰብዓዊና ቁሳዊ እንዲሁም ስነ ልቦናዊ ጉዳት ደርሶበታል ብለዋል።
አሁን ላይም በዞኑ የተገኙት የልማት ቱርፋቶች ሁሉ የሠራዊቱና የፀጥታ ኀይሉ የመስዋዕትነት ውጤት መሆናቸውን የጠቆሙት ዋና አዛዡ በቀጣይም የተቀናጀ የፀጥታ ሥራ በመሥራት ሰላሙን ማፅናትና የተገኙትን መልካም እድሎች መጠቀም እንደሚገባ አፅንኦት ሰጥተዋል።
የምስራቅ ጎጃም ዞን ምክትል አስተዳዳሪ ዋለ አባተ በበኩላቸው ፅንፈኛ ቡድኑ እኩይ አላማውን ለማሳካት ሕዝቡን በተለያዩ መንገዶች ቅስቀሳ ቢያደርግም ሕዝቡ ለሰላም ባለው ፅኑ ፍላጎት ጥረቱ እንደከሸፈበት አስረድተዋል።
ሠራዊቱ ሕዝባዊ ባሕሪውን ጠብቆ እየፈፀመ በሚገኘው የሕግ ማስከበር ዘመቻ የዞኑ ሰላም ተመልሷል ያሉት አቶ ዋለ የዘመናት የልማት ጥያቄዎች ሁሉ ምላሽ እያገኙ እንደሆም አንስተዋል።
ዞኑ አሁንም ቢሆን ውስጣዊ አቅሙን በማጠናከር የተገኘው ሰላም እንዳይቀለበስ በትኩረት መስራት እንደሚገባ ለዞንና ለወረዳ የሥራ ኀላፊዎች አስገንዝበዋል። ዘላቂ ሰላምን ለማፅናት ከሠራዊቱ ጋር ተቀናጅቶ መሥራት እንደሚያስፈልግም ምክትል አስተዳዳሪው አመላክተዋል። መረጃው የሀገር መከላከያ ሠራዊት ነው።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
