ሁሉንም ተማሪዎች ያሳለፈው ማዕከል የስኬት ሚስጥር ምንድን ነው?

14
የባሕር ዳር ሳይንስ ኢንኩቤሽን ማዕከል ተማሪዎቹን በየዓመቱ የሚሰጠውን የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ሙሉ በሙሉ የማሳለፍ እና የላቀ ውጤት የማስመዝገብ ባሕሉን አጠናክሮ ቀጥሏል።
🧑‍🎓 ጥብቅ የማጣሪያ ፈተና
የማዕከሉ ዳይሬክተር ዓለሙ ተስፋዬ (ዶ.ር) ከአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ጋር ባደረጉት ቆይታ ለዚህ ተከታታይ ስኬት መሠረት ከኾኑት ዋና ዋና ምክንያቶች መካከል ብቃት ተኮር የተማሪዎች ቅበላ አንዱ እንደኾነ ተናግረዋል። ተማሪዎች ወደ ማዕከሉ የሚገቡት ጥብቅ የማጣሪያ ፈተና አልፈው ነው ብለዋል። ተማሪዎቹም ከመነሻው የተሻለ የማሰብ እና የመማር አቅም ያላቸው መኾናቸውንም አመላክተዋል።
📝ተማሪ ተኮር የማስተማር ስልት
ሌላው የስኬት መሠረት ተማሪ ተኮር እና የተግባር የመማር ሂደት እንደኾነ ገልጸዋል። ከአብዛኞዎቹ መደበኛ የትምህርት ቤቶች የአንድ ክፍለ ጊዜ ርዝማኔ በተለየ ሁኔታ በስቲም ሴንተሩ ሙሉ 1 ሰዓት እንደሚመደብ ተናግረዋል። ይህም መምህራን ይዘቶችን በበቂ ሁኔታ እንዲሸፍኑ እና ተማሪዎች ከተራ የቀለም ትምህርት ወጥተው እንዲያስቡ ያግዛል ነው ያሉት።
ተማሪዎች ገና ከ9ኛ ክፍል ጀምሮ እስከ 11ኛ ክፍል ድረስ በፈጠራ ሥራዎች፤ ፕሮጀክቶች እና ልዩ ልዩ ውድድሮች እንዲሳተፉ በመደረጉ የማሰብ አድማሳቸው እንዲሰፋ አድርጓል፤ ይህም ጥሩ ውጤት ለማስመዝገብ ምክንያት ኾኗል ነው ያሉት። ተማሪዎች 12ኛ ክፍል ላይ የፈጠራ ፕሮጀክቶችን አቁመው ሙሉ ትኩረታቸውን በቀለም ትምህርቱ ላይ እንዲያደርጉ ይደረጋልም ብለዋል። የሚማሩትም በከፍተኛ ትምህርት ተቋም መምህራን መኾኑንም ጠቅሰዋል።
📌ጠንካራ የምዘና ሥርዓት
ጠንካራ የምዘና ሥርዓት ሌላው ተደጋጋሚ ስኬት ለማስመዝገብ ያስቻላቸው ተግባር መኾኑን ተናግረዋል። ከከተማ አሥተዳደሩ ሞዴል ፈተና በተጨማሪ ማዕከሉ ከ9ኛ እስከ 12ኛ ክፍል ያሉ ይዘቶችን ያካተተ ቢያንስ ሁለት ዙር ሙሉ የሞዴል ፈተናዎችን ይሰጣል ብለዋል። የምዘና ፈተናዎቹን ተከትሎ የሚሰጠው ግብረመልስ ተማሪዎች ክፍተታቸውን አውቀው በበቂ ሁኔታ እንዲዘጋጁ የሚያደርግ መኾኑን አንስተዋል።
ማዕከሉ በቀጥታ ተማሪዎችን አፈላልጎ ወደ ውጭ ሀገር የሚልክበት ተቋማዊ አሠራር እንደሌለው የተናገሩት ዳይሬክተሩ ተማሪዎች በማዕከሉ የሚያገኙት የላቀ የቴክኖሎጂ፣ የፈጠራ፣ የጽሑፍ እና የቃለመጠይቅ ብቃት ተጠቅመው በራሳቸው ጥረት ወደ አሜሪካ፣ ካናዳ፣ ጣሊያን እና ልዩ ልዩ የአፍሪካ ሀገራት የትምህርት ዕድል አግኝተው መሄድ ችለዋል ነው ያሉት። ይህ ሲታሰብ ጥቅምም ጉዳትም ይኖረዋል ብለዋል።
📌የተማሪዎችን ቁጥር የማሳደግ እቅድ
የወላጆች እና የተማሪዎች ፍላጎት በከፍተኛ ሁኔታ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በመምጣቱ አሁን ላይ በላቦራቶሪ ውስጥ እየተካሄደ ያለውን መማር ማስተማር ወደ ሰፊ ክፍሎች ለማዛወር ዕቅድ እንዳለም ተናግረዋል። የተማሪዎችን ቅበላ አቅም ለማሳደግም ከባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ጋር ውይይቶች እየተደረጉ እንደሚገኙ አንስተዋል።
ማዕከሉ በአጠቃላይ ከ9ኛ እስከ 12ኛ ክፍል ከ190 እስከ 200 የሚደርሱ ተማሪዎችን በ2019 የትምህርት ዘመን የማስተማር ዕቅድ እንዳለው አመላክተዋል።
✍️ ዘጋቢ፦ ሮዛ የሻነህ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleእውነት የማትሞትበት የዋርካው ጥላ።