
የሰማዩ ገጽ በጠቆረ ደመና ሲሸፈን መሬቱ የዝናብ ጠብታ እንደሚናፍቅ ሁሉ የሰው ልጅም በኑሮ ውጣ ውረድ የሚሻከረውን የሰዎች ግንኙነት የሚያድስ እና የሰላም ድልድይን የሚገነባ ታላቅ የጥበብ ድር አለ። ይኽውም ከጥንት አባቶቻችን የወረስነው እና የኢትዮጵያዊነት ማህተም የኾነው ሽምግልና ነው።
በግዙፍ የዋርካ (ትልቅ) ዛፍ ጥላ ስር፣ የዘመንን ውጣ ውረድ በተሻገሩ እና ጸጉራቸው በጥበብ ጸዳል በነጣ አረጋውያን የሚመራው ይህ የዕርቅ ሥርዓት የተበጠሰውን የሕይወት ክር በማሰር የሰላም እና የፍቅርን እስትንፋስ ዳግም የሚመልስ የነፋስ ቋንቋችን ነው።
አበው ዕውቀታቸውን በቃል አኖሩት፤ ፍልስፍናቸውን በምሳሌ ቋጠሩት። “የማይፈስ ውኃ አይጋጭም” በማለት አብሮ መኖር ግጭት እንዳለው ነገር ግን መጣላት ሐጢያት እንዳልኾነ እና ቂም ማቆየት ግን እንደሚያቆስል በቅኔያዊ ንግግራቸው ያስተምራሉ።
በመሐል የተቋጠረውን፣ የተሰበረውን፣ የደማውን እና የሻከረውን ልብ ለማከም ክብር የሽምግልና መሠረት ይኾናል። አባቶች በክብራቸው እና በነጭ ጸጉራቸው ይታፈራሉ። ቃላቸው እንደ ማለዳ ጠል፣ ድምጻቸው እንደ ጸደይ ወፍ ዝማሬ ልብን የሚያርስ ነው።
“በለስላሳ አንደበት፣ አጥንት ይሰበራል” እንዲሉ የሽማግሌ ቃል ለስላሳ ኾኖ ሳለ ውስጠቱ ግን የታበየውን አንገት የሚያስደፋ እና የደነደነውን ልብ የማፍረጥረጥ ብርታት አለው። ጩኸት እና ዛቻ ሳይኖር እርጋታቸው ድንጋይ ያቀልጣል።
በዕርቅ ሂደቱ ውስጥ እውነት እና ፍትሕ መሪ ሚና አላቸው። ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም ሽማግሌ እና ሽምግልና በሚለው መጽሐፋቸው እንዳሰፈሩት እውነተኛ ሽማግሌዎች ለማንም ኅይል ሳያደሉ እውነትን አፍርጠው በመናገር በዳይን አሳምነው እና በደልን አሳውቀው ዘላቂ የልብ ዕርቅ የሚያመጡ አድባር ናቸው።
“በሽማግሌ ፊት እውነት አትሞትም” እንደሚባለው ውሸት ቦታ የላትም፣ እውነት ትነጥራለች። ጥፋት በቁጣ ሳይኾን በማስተዋል፣ ክስ በወቀሳ ሳይኾን በመመካከር ይመረመራል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በአማርኛ ቋንቋ፣ ሥነ ጽሑፍ እና ፎክሎር ትምህርት ክፍል በኤልያስ ወላንሳ ሀብተየስ “ባሕላዊ የግጭት አፈታት ሥርዓት በሃላባ ብሔረሰብ” በሚል ርዕስ የተሠራው ጥናት ባሕላዊ የግጭት አፈታት ሥርዓቶች ማኅበረሰባዊ ተቀባይነት ያላቸው፣ ፈጣን፣ የተደበቁ እውነታዎችን አውጥተው ከቂም የጸዳ ዘላቂ ሰላምን የሚያሰፍኑ መኾናቸውን አረጋግጧል።
የሽምግልና ሥርዓት የብቀላ ስሜቶችን በማስቀረት፣ ግጭቶች ወደ ደም መፋሰስ እንዳያመሩ ፈጥኖ ጣልቃ በመግባት፤ በዳዮችን በማቅረብ ጥፋቱ ኾን ተብሎ ወይም በስህተት የተፈጸመ መኾኑን በመለየት እንደየጥፋታቸው ክብደት ተገቢውን ባሕላዊ ቅጣት እንዲያገኙ በማድረግ የኅብረተሰቡን ሰላም በዘላቂነት ይጠብቃሉ።
ሽምግልና እንደ ፍርድ ቤት አንዱን አሸናፊ ሌላውን ተሸናፊ አያደርግም፤ ሁለቱንም የሰላም አሸናፊ ያደርጋቸዋል። “ሰማይ ተቀደደ ቢሉት ሽማግሌ ይሰፋዋል” የተባለውም ለዚህ ነው። የቱንም ያህል በደል ይክበድ፣ ቂም እንደ ተራራ ይገዘፍ፤ የሽማግሌ ልብ ግን ይሰፋዋል።
በእጃቸው የያዙት እርጥብ ሳር የሕይወት እና የተስፋ ተምሳሌት ኾኖ “እርጥብ ይሁን መንገዳችሁ” ሲሉ ምርቃታቸው እንደ በጋ ዝናብ በደረቀው ልብ ላይ ይወርዳል። የተቋጠሩ ፊቶች በፈገግታ ይፈካሉ፤ የክፋት ቃል በይቅርታ ይተካል፤ ወንድም ከወንድሙ፣ እህት ከእህቷ ይታረቃሉ።
ይህ የነፍስ ህክምና ከግለሰብ አልፎ ለሀገር ህልውና ወሳኝ ነው። የፖለቲካ ቁርሾ በጠመንጃ እና በጉልበት አይፈታም፤ ጠመንጃ አካልን እንጂ ልብን ሊያሸንፍ አይችልም። በአሸናፊ እና ተሸናፊ ሥሌት መጓዝም ዘላቂ መፍትሔ አያመጣም።
የሰላም ሚኒስትር የሽምግልና ሥርዓት ግጭትን ከመፍታት ባለፈ ቤተሰብን እና ጠንካራ ማኅበረሰብን ለመገንባት የሚያገለግል፣ ከብሔር እና ከሃይማኖት በላይ የኾነ ሀገራዊ የትስስር እሴት መኾኑን አስምሮበታል።
ዘጋቢ፦ስማቸው አጥናፍ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
