
የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን በዓለም ዓቀፍ መድረክ የአፍሪካን ጥቅሞች ለማስጠበቅ መሥራቱን እንደሚቀጥል የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ማህሙድ አሊ የሱፍ ተናግረዋል። ሊቀመንበሩ ይህንን ያሉት የአፍሪካ ኅብረት የሥራ አሥፈጻሚዎች ምክር ቤት 49ኛው መደበኛ ሥብሠባን በከፈቱበት ወቅት ነው።
ለሁለት ቀናት የሚቆየው የሥራ አሥፈጻሚዎች ምክር ቤት ሥብሠባ እየተካሄደ ያለው የአፍሪካ ኢኮኖሚ ላይ ቀጥተኛ ተጽዕኖ የሚያሳድሩ ውሥብሥብ ዓለም አቀፍ የጂኦፖለቲካዊ ሁነቶች በተፈጠሩበት ወቅት እንደኾነ ገልጸዋል። በተለይ በመካከለኛው ምሥራቅ ያለውን ሁኔታ እና በአህጉሪቱ ላይ እያሳደረ ያለውን ተፅዕኖ በተመለከተ ኮሚሽኑ ችግሩን በቅርብ እየተከታተለ መኾኑን ተናግረዋል።
በተጨማሪም ኮሚሽኑ በውሳኔ አሰጣጥ ግልጽነት ለመፍጠር እና ተገቢውን የጋራ ምላሽ ለማስተዋወቅ ለኅብረቱ ፖለቲካዊ አካላት መደበኛ ትንተና ማቅረቡን እንደሚቀጥል ገልጸዋል።
ሰላም እና ደኅንነትን በተመለከተ በበርካታ የአፍሪካ ቀጣናዎች የሽብርተኝነት እና የጽንፈኝነት መሥፋፋት ስጋት እንዳሳደረባቸው ገልጸዋል።
በቅርቡ በሳህል ሀገራት ያደረጉትን ጉብኝት በማስታወስ አባል ሀገራት እነዚህን የጋራ የደኅንነት ፈተናዎች ለመቋቋም በሚያደርጉት ጥረት የአፍሪካ ኅብረት የሚያደርገውን ያልተቋረጠ ድጋፍ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።
በዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ያለውን የኢቦላ ወረርሽኝ አሳሳቢነት በመረዳት ለኮንጎ ሕዝብ እና መንግሥት ድጋፉ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
በተጨማሪም የአፍሪካ የበሽታዎች መቆጣጠሪያ እና መከላከል ማዕከል (አፍሪካን ሲዲሲ) ከሀገሪቱ ባለሥልጣናት እንዲኹም ከቀጣናው እና ዓለም ዓቀፍ አጋሮች ጋር በመቀናጀት አህጉራዊ ምላሹን በማስተባበር ላይ እንደሚገኝ አመላክተዋል።
ዘጋቢ: መሠረት መቅጫ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
