“ወገኖቻችን በግልጽነት፣ እየተከባበሩ፣ እየተቀራረቡ እና እየተነጋገሩ ነው” ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ

6
ኢትዮጵያ እየመከረች ነው። የምክክር ጉባዔ ማድረግ ከጀመረች ሰነባብታለች። የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የእስካሁኑን ሂደት አስመልክቶ መግለጫ ሰጥቷል።
መግለጫውን የሰጡት የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ ሀገራዊ ምክክሩ ሂደቱን ጠብቆ እየተካሄደ መኾኑን ገልጸዋል።ተሳታፊዎቹ ተማምነው እየሄዱ ነው ብለዋል።
እስር አስር አራት መቶ ቦታ፣ ሃምሳ ሃምሳ ሰማንያ ቦታ ኾነው ሲወያዩ መቆየታቸውን አንስተዋል። አሁን ላይ በሚገባ እየተሰነዱ ወደ 250 ወይም ስልታዊ ቡድን ወደሚባለው እየተሸጋገረ መኾኑን ገልጸዋል።
ሃሳቦች በሚገባ ቀርበዋል፤ አንዳንድ ሰዎች አልቋል እንደሚሉት ግን አይደለም፤ ያለቀ ነገር የለም፤ የመጡት ሃሳቦች ሁሉ ቀስ በቀስ እየተቀራረቡ ነው ብለዋል።
“እንደዚህ ተወሰነ” እየተባለ የሚወራው ዝም ብሎ ነው፤ የተወሰነ ነገር የለም ነው ያሉት። በዚህ ሳምንት የስልታዊ ምዕራፍ አልቆ በሚቀጥለው ሳምንት ወደ አምስት መቶው እንደሚሸጋገሩ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።
ግብዓቶቹ በሚገባው እየተሰነዱ ነው፤ ሰነዶቹ በተገቢው ካልተነሰዱ ውጤቱ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ይኖረዋል፤ ታሪክም ነው፤ ይሄን ታሳቢ በማድረግ ሰነዶቹ በሚገባው እየተሰነዱ ነው ብለዋል።
ተሳታፊዎች በሚገባው ተሳትፎ በማድረግ ይሄን ታሪካዊ ሂደት ጥሩ ደረጃ ላይ ማድረስ እንደሚገባቸው አስገንዝበዋል። የምክክሩ ዓላማ ትንሽ ቁጥር ያላቸው የማኅበረሰብ ክፍሎች ትልቅ ቁጥር ካላቸው የማኅበረሰብ ክፍሎች ጋር በእኩልነት እንዲነጋገሩ ማድረግ ነው፤ ብዙ ኾኖ መጥቶ እጅ አውጥቶ አሸንፎ ለመሄድ አይደለም፤ እኩል ኾነን መግባባት ላይ እንድንደርስ እና በእኩልነት አሸናፊ ኾነን እንድንወጣ ማድረግ ነው አላማው ብለዋል።
ምክክር በድምጽ ብልጫ የሚወሰንበት ሳይኾን እየተግባቡ መሄድ እንደኾነ ገልጸዋል። በምክክር አንደኛው ሌላኛውን ተጭኖ የሚወጣበት እንዳልኾነ ነው የተናገሩት። በምክክር ሂደቱ ችግር ሲፈጠር ችግሩን የሚፈታ ራሱን የቻለ ቡድን እንዳለም ገልጸዋል።
ወገኖቻችን በግልጽነት፣ እየተከባበሩ እና እየተቀራረቡ እየተነጋገሩ ነው ብለዋል። ብዙ መከባበር ያለበት ሂደት መኾኑንም ተናግረዋል። የምክክር ሂደቱ እስካሁን ስኬታማ መኾኑን አንስተዋል።
የእኔ የሚለው ሃሳብ ቀስ በቀስ እየወጣ የእኛ ሃሳብ ወደሚለው እየቀረበ ነው ብለዋል። ዓመቱ ከመጠናቀቁ በፊት ወደ ምክረ ሃሳብ ደርሰን በአዲሱ ዓመት ትልቅ ብሥራት እንደምንሰማ ተስፋ እናደርጋለን ነው ያሉት።
ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous article‎የሀረሪ ክልል ትምህርት ቢሮ የትምህርት ጥራትን ለማጎልበት በትኩረት እንደሚሠራ ገለጸ።
Next article“ኮሚሽኑ በዓለም አቀፍ መድረክ የአፍሪካን ጥቅሞች ለማስጠበቅ መሥራቱን ይቀጥላል” የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ማህሙድ አሊ የሱፍ