‎የሀረሪ ክልል ትምህርት ቢሮ የትምህርት ጥራትን ለማጎልበት በትኩረት እንደሚሠራ ገለጸ።

5
በ2019 በጀት ዓመት የትምህርት ጥራትን ይበልጥ ለማጎልበት በትኩረት እንደሚሠራ የሀረሪ ክልል ትምህርት ቢሮ ምክትል ኀላፊ አርሰናል አብዲ ገልጸዋል።
የሀረሪ ክልል ትምህርት ቢሮ በበጀት ዓመቱ በሚከናወኑ ጉዳዮች ዙሪያ መግለጫ ሰጥቷል። በመግለጫውም በያዝነው የበጀት ዓመት የትምህርት ጥራትን ይበልጥ በማጎልበት ሁሉን አቀፍ ሥራዎች በትኩረት እንደሚሠሩ ተገልጿል።
ዘርፉን ይበልጥ ውጤታማ ለማድረግ የትምህርት ዘርፉን ሪፎርም ከማድረግ ጀምሮ የመምህራን እና ትምህርት መሪዎችን አቅም ለማጎልበት ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሠራም ተመላክቷል።
በተለይ በትምህርት ለትውልድ ንቅናቄ የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ለማሻሻል ብሎም በግብዓት እንዲደራጁ የማድረግ ሥራ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሠራ ተጠቁሟል።
በትምህርት ቤቶች የተጀመሩ የተማሪ ምገባ መርሐ-ግብርን በማጎልበት የተማሪዎች የመጠነ ማቋረጥ እና መቅረት ምጣኔን በመቀነስ የትምህርት ቅበላ አቅምን ለማሳደግም እንደሚሠራ ተገልጿል።
ለዚህም በክልሉ በከተማ እና በገጠር የሚገኙ 40 ሺህ ተማሪዎችን የምገባው ተጠቃሚ ለማድረግ 46 ሚሊዮን ብር መመደቡ ነው የተብራራው።
በሌላ በኩል በግል ትምህርት ቤቶች ከማኅበረሰቡ ለሚነሱ ቅሬታዎች አስፈላጊውን ክትትል በማድረግ ለማረም እንደሚሠራም ተጠቁሟል።
በተጨማሪም የትምህርት መሠረተ ልማቶች፣ የመማሪያ ፋሲሊቲዎች እና የዲጂታል ቴክኖሎጂ አጠቃቀምን በማሻሻል የመማር እና የማስተማር ሂደትን ዘመናዊ፣ ተደራሽ እና ውጤታማ እንዲኾን ይደረጋል ተብሏል።
በሦሥቱ የገጠር ወረዳዎች ከቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶች ጀምሮ የአንደኛ እና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ግንባታ እንደሚከናወን የገለጹት ምክትል ኀላፊው በክልሉ እየተገነባ የሚገኘው ሞዴል የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በቀጣይ መስከረም/2019 ዓ.ም ሥራ ለማስጀመር ርብርብ እየተደረገ ነው ብለዋል።
የተማሪ ውጤትን ለማሻሻል ከቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ጀምሮ ትኩረት መደረጉን የገለጹት አቶ አርሰናል የመማሪያ መጽሐፍ ስርጭት ምጣኔን በተመለከተም ከቅድመ መደበኛ እስከ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች 1 መጽሐፍ ለ1 ተማሪ ተደራሽ እንደሚደረግ ተናግረዋል።
የልዩ ፍላጎት እና የጎልማሶች ትምህርትን ጨምሮ ሁሉም ተማሪዎች ተገቢ፣ ጥራት ያለው፣ ፍትሐዊ እና ተደራሽ ትምህርት እንዲያገኙ በማድረግ በዕውቀት፣ በክህሎት እና በመልካም ሥነ ምግባር የተገነቡ እንዲሁም ለሥራ እና ለሀገር ግንባታ ዝግጁ የኾኑ ዜጎችን ለማፍራት እንደሚሠራም ተመላክቷል።
በተለይም በ6ኛ፣ በ8ኛ እና በ12ኛ ክፍል የሚደረጉ ክልላዊ እና ሀገራዊ ፈተናዎችን የማለፍ ምጣኔን የበለጠ ለማሳደግ በመማር ማስተማር፣ በትምህርት ድጋፍ እና ክትትል ላይ ልዩ ትኩረት ይሰጣል ተብሏል።
በበጀት ዓመቱ ከቅድመ መደበኛ እስከ ሁለተኛ ደረጃ 91 ሺህ 411 ተማሪዎች ተመዝግበው ትምህርታቸውን ይከታተላሉ ተብሎ ይጠበቃል ሲሉ ምክትል ኀላፊው ገልጸዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous article‎ከጣውላ የኤሌክትሪክ ማከፋፈያ የሠራው ወጣት።