‎ከጣውላ የኤሌክትሪክ ማከፋፈያ የሠራው ወጣት።

2
‎በምዕራብ ጎጃም ዞን ሰከላ ወረዳ የተወለደው ወጣት አብነህ አቻምየለህ የፈጠራ ክህሎቱን የጀመረው ገና በልጅነቱ ነበር። በተለይም ወደ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ሲያልፍ የወደቁ የኤሌክትሪክ ዕቃዎችን በመጠገን የጀመረው ጉዞ በኋላ ላይ የፈጠራ ሥራውን እንዲያሰፋ ትልቅ መንገድ ከፍቶለታል።
‎ሥራ አጥነትን በፈጠራ እና በትግል ማለፍ እንደሚቻል በተግባር ያረጋገጠው ወጣቱ ከጣውላ የሠራቸውን የኤሌክትሪክ ማከፋፈያዎች (ዲቫይደሮች) ወደ ገበያ ማስገባት ችሏል።
‎ወጣቱ መጀመሪያ ላይ ያገለገሉ የፕላስቲክ «ኪቶ ጫማ» ሶሎችን በመሠብሠብ ለኮምፒውተር እና ለተለያዩ የኤሌክትሪክ ዕቃዎች ማከፋፈያ የሚኾኑ ዲቫይደሮችን ይሠራ እንደነበር ተናግሯል፡፡ በሂደትም ወደ ሀገር በቀሉ ጣውላ በመቀየር ጥራታቸው የተረጋገጡ ምርቶችን ማምረት ጀምሯል።
‎ወጣት አብነህ ከዩኒቨርሲቲ በስፖርት ሳይንስ የመጀመሪያ ዲግሪውን ከተመረቀ በኋላ ሥራ ከመፈለግ ይልቅ እጁ ላይ ያለውን የፈጠራ ክህሎት ወደ ገቢ ምንጭነት ለመቀየር ችሏል።
“ዩኒቨርሲቲ ከመግባቴ በፊት የጀመርኩት ሥራ ስለነበር፣ ከተመረቅኩ በኋላ በሥራ ፍለጋ ጊዜዬን ከማቃጠል ይልቅ ይህንኑ ፈጠራዬን ብሠራ የተሻለ እንደኾነ አምኜ እየሠራሁ ነው” ብሏል።
‎የጣውላ የኤሌክትሪክ ማከፋፈያ (ዲቫይደሮቹ) በገበያ ላይ ከሚገኙት የቻይና የፕላስቲክ ማከፋፈያዎች በግማሽ ዋጋ ቀንሰው የሚሸጡ በመኾኑ ተመራጭ አድርጓቸዋል ነው ያለው።
ገበያ ላይ ያሉ የፕላስቲክ ማከፋፈያዎች ከ650 እስከ 800 ብር ሲሸጡ እርሱ የሚያመርታቸው ግን ከ350 እስከ 400 ብር እንደሚያቀርብ ነው የገለጸው፡፡
‎ከዋጋቸው አነስተኛነት ባሻገር ምርቶቹ አይቀልጡም፤ በቀላሉ አይበላሹም ነው ያለው፡፡ የውስጥ መስመሮቻቸው በጠንካራ የኤሌክትሪክ ገመዶች የተያያዙ በመኾናቸው እንደ ሌሎቹ የውጭ ሀገር ምርቶች በጊዜ ሂደት የመላላት ችግር የለባቸውም ብሏል።
‎በፕላስቲክ የኤሌክትሪክ ማከፋፈያ (ዲቫይደሮች) መጠቀም የማይቻለውን የኤሌክትሪክ ምድጃ (ስቶቨ)ሳይቀር የመሸከም አቅም እንዳላቸው ተናግሯል፡፡
ምርቱ ረጅም የአገልግሎት ዘመን ያለው በመኾኑ እስከ ሰባት ዓመታት ያለ ምንም ብልሽት አገልግሎት መስጠት እንደሚችልም አንስቷል።
‎በምርቶቹም በቲሊሊ፣ እንጅባራ፣ ፍኖተ ሰላም፣ ደብረ ማርቆስ እና ባሕር ዳር ከተሞች ሰፊ ደንበኞችን ማፍራት እንደቻለም ጠቁሟል፡፡ ምርቱን የተጠቀሙ ደንበኞችም የማይላላ እና ለረጅም ጊዜ አገልግሎት እየሰጣቸው መኾኑን ገልጸዋል፡፡
‎ወጣቱ በቀጣይም የፈጠራ ሥራዎቹን ወደ ተለያዩ ዘርፎች በማስፋት፣ የኅብረተሰቡን ችግር የሚፈቱ አዳዲስ ሥራዎችን ለማቅረብ አልሞ እየሠራ መኾኑን ገልጿል።
ዘጋቢ፡- ፍሬሕይወት አዘዘው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleየሕገ ወጡ ሕወሃት ቡድን የደም ማፍሰስ ፖለቲካ ይ
Next article‎የሀረሪ ክልል ትምህርት ቢሮ የትምህርት ጥራትን ለማጎልበት በትኩረት እንደሚሠራ ገለጸ።