የሕገ ወጡ ሕወሃት ቡድን የደም ማፍሰስ ፖለቲካ ይ

4
🛑🕊️
ሕገወጡ የሕወሃት ቡድን ከተመሠረተበት ጊዜ አንስቶ ፖለቲካዊ ፍላጎቱን በግፍ እና በደም ማፍሰስ ላይ የመሠረተ፣ ለሕዝብ ሕይወት ዋጋ የማይሰጥ ጸረ ሰላም ነው።
በተለይም በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል በጫረው ጦርነት ምክንያት ሕዝብ አሰቃቂ መከራን እንዲቀበል አድርጓል። በርካታ እናቶች ልጆቻቸውን እና ባለቤታቸውን እንዲያጡም አድርጓል። የወጣቶችን ሕይወትም ለከንቱ የፖለቲካ ፍላጎቱ ሲጠቀም ቆይቷል አሁንም እየተጠቀመ ይገኛል።
“ነገ ይጦረኛል” ብለው ያሳደጓቸውን ልጆቻቸውን በግፍ ያጡ እናቶች አንጀት እንዲቆስል እና የትግራይ ክልልን ያለ ወጣት ለማስቀረት የሚኳትን ቡድን ነው። ይህ ሕገወጥ ቡድን ሰላም እና ጸጥታን ለማናጋት የሚሠራ ቡድን መኾኑ ከማንም የተሰወረ አይደለም።
ይህ ቡድን ዛሬም ዳግም ሌላ ቁስል ለመፍጠር እና ትውልድን ለማጥፋት የሚያደርገውን እኩይ እንቅስቃሴ በጋራ መታገል የሁሉም የዜግት ግዴታ ሊኾን ይገባል።
በእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ፍልስፍና መምህር ዓለምነህ አጋዤ ሕገወጡ ሕወሃት ከተመሠረተበት ጊዜ አንሥቶ የትግል ጉዞው በጦርነት እና በግጭት የፖለቲካ ፍልስፍና ላይ የተመሠረተ መኾኑን ነው የገለጹት።
ቡድኑ ከመንግሥት ጋር በቅንጅት ከመሥራት ይልቅ የሀገሪቱን የፖለቲካ ምህዳር ወደ ቀውስ የሚዳርግ የጠብ አጫሪነት ባሕሪን መከተሉን አስገንዝበዋል።
ይህ ደግሞ ኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ምክክሮችን እያደረገች ባለችበት በዚህ ወሳኝ ወቅት ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ በውይይት በጠረጴዛ ዙሪያ የመፍታት አማራጭ እያለ ጠብ አጫሪነትን እና ግትር ፖለቲካን ማራመድ አግባብ አይደለም ነው ያሉት።
ያም ኾኖ የጦርነት ነጋሪት መጎሰሙ ሀገርን የሚጎዳ ጸረ ሰላም አካሄድ ነው ይላሉ። ቡድኑ የፕሪቶሪያን የሰላም ስምምነት በማፍረስ ወደ ጦርነት ማቅናቱ በሀገሪቱ ፖለቲካ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ያሳድራልም ብለዋል።
ባለፉት ዓመታት ሕገወጥ ቡድኑ በሀብት፣ በንብረት እና በሰው ሕይወት ላይ ከፍተኛ ውድመት አስከትሎ እንደነበር አውስተዋል። በተለይም የትግራይ ሕዝብን ለከፍተኛ ስቃይ እና እንግልት ዳርጓል ነው ያሉት። እናቶችን ጥቁር ማቅ አልብሷል፣ ያለጧሪ እና ቀባሪ አስቀርቷልም ብለዋል።
ወጣቶችን የጦርነት ሲሳይ አድርጎ የትውልድ ጠባሳ ማስቀመጡንም አብራርተዋል።
ሕገወጡ ቡድን ዘር ተኮር ጥቃት፣ ሕገወጥነት፣ ግጭት እና የሥልጣን አምባገነናዊ ፍላጎት የፖለቲካ መገለጫዎቹ ናቸው ያሉት መምህሩ የሀገሪቱን የፖለቲካ ምህዳር ወደ ኋላ በመጎተት የልማት እና የሰላም ማነቆ መኾኑን ነው ያስረዱት።
ሕገወጡ ቡድን የሚሠራውን ሴራ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ያውቀዋል ያሉት መምህሩ ይህ ደግሞ አካሄዱ አምባገነናዊ መኾኑን ያሳያል ነው ያሉት። ለሕዝብ ጥቅም ሳይኾን ለራሱ ሥልጣን የሚታገል ቡድን እንደኾነም ጠቁመዋል። ይህን ሕገ ወጥ ቡድን ለማምከን የመንግሥት ሆደ ሰፊነት ሊበቃ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
ማንም አካል ከሕግ በላይ አይደለም ያሉት መምህሩ መንግሥት የዜጎችን ደኅንነት እና ሰላም የማስጠበቅ ግዴታ አለበት ነው ያሉት። ሀገርን የሚያውኩ ሕገወጥ ቡድኖችን የመቆጣጠር ኀላፊነቱን ሊወጣ ይገባልም ብለዋል።
መምህሩ እንደተናገሩት የትግራይ ወጣቶች እና ሕዝቡ ሕገወጡ የሕወሃት ቡድን ለዓመታት ከጦርነት እና ከስቃይ ውጭ ምንም ዓይነት ጥቅም እንዳላመጣላቸው ተገንዝበው የቡድኑን ጸረ ሰላም አካሄድ አጥብቀው ሊያወግዙ እና “ጦርነት ይብቃ ” ማለት ይኖርባቸዋል። እስከ መቼ ድረስ ጦርነት ይቀጥላል ? ወጣቱ ትውልድስ እንዴት ያለአግባብ ያልቃል? ማለት አለባቸው ነው ያሉት።
በተለይም የአፋር፣ የትግራይ እና የአማራ ክልል ሕዝቦች የሕገወጡን ቡድን ድርጊት በጋራ በመቃወም ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ጋር በመኾን ሀገር የማፍረስ አጀንዳውን ሊመክቱ እንደሚገባ ነው ያስገነዘቡት።
ለዓመታት የኢትዮጵያን ሕዝብ ማቁሰል፣ ማፈናቀል እና የሀገር ሀብት ማውደም እንጂ ምንም ዓይነት በረከት ያላመጣውን ይህንን ሕገ ወጥ ቡድን ለማስቆም መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ በአንድነት ሊቆም እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleየምሥራቅ ዕዝ ሬጅመንት በወንበርማ ወረዳ ከሕዝቡ ጋር በመቀናጀት የመንገድ ጥገና በጎ አድራጎት ሥራዎችን አከናወነ።
Next article‎ከጣውላ የኤሌክትሪክ ማከፋፈያ የሠራው ወጣት።