
በምዕራብ ጎጃም ዞን በወምበረማ ወረዳ ቡሪፋር ቀበሌ የተበላሹ መንገዶችን በመጠገን ሕዝቡ የተሻለ የመጓጓዣ አገልግሎት እንዲያገኝ የአንድ ኪሎ ሜትር የመንገድ ጥገና ሥራ በመከላከያ ሠራዊት ተሠርቷል።
የምሥራቅ ዕዝ ሬጅመንት አዛዥ ሻምበል አወል ሰዒድ ሬጅመንቱ ከግዳጅ ጎን ለጎን ከወረዳው አሥተዳደር እና ከአካባቢው ማኅበረሰብ ጋራ በመተባበር የተበላሹ መንገዶችን በማስተካከል ለሕዝቡ የተሻለ አገልግሎት እንዲያገኝ አስችሏል ብለዋል።
የወረዳው ኮሙዩኒኬሽን ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አወቀ መሰረት የመንገድ ጥገና ሥራዎቹ የሕዝቡን የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ በማሳለጥ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳላቸው ተናግረዋል።
በመከላከያ ሠራዊት እና በማኅበረሰቡ የጋራ ትብብር መከናወኑ ለቀጣይ ልማት ጠንካራ መሠረት የጣለ መሆኑንም ገልጸዋል።
የአካባቢው ነዋሪዎችም የመንገድ ጥገናው የመጓጓዣ ችግራቸውን በመቅረፍ ለኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ እንቅስቃሴያቸው ከፍተኛ እገዛ እንዳደረገላቸው ገልጸዋል። ሠራዊቱ ለማኅበረሰቡ እያደረገላቸው ያለውን ድጋፍም አድንቀዋል። የሀገር መከላከያ ሠራዊት ሕግን ከማስከበር ጎን ለጎን የሚያከናውናቸው የልማት ሥራዎች ሠራዊቱ ለሕዝብ እና ለሀገር የቆመ ዋነኛ አጋር መኾኑን የሚያሳይ ተግባር ነው።
ዘገባው የምስራቅ ዕዝ ነው።
#ባሕርዳር ሐምሌ 21/2018 ዓ.ም
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
