ሀገራዊ ምክክሩ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም መከበር ምን አበርክቶ ይኖረዋል?

6
🇪🇹🗣️
💡🤝
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ለሀገሪቱ ብሔራዊ ጥቅም መከበር የሚኖረው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው። ብሔራዊ ጥቅም የሀገርን ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት ማስጠበቅን፣ የዜጎችን ደኅንነት ማረጋገጥን፣ የኢኮኖሚ ብልጽግናን ማምጣት እና በዓለም አቀፍ መድረክ ላይ ጠንካራ የዲፕሎማሲ አቅም መገንባትን ያጠቃልላል። እነዚህን ግቦች ለማሳካት የውስጥ ፖለቲካዊ መረጋጋት እና የጋራ ማኅበራዊ ስምምነት መኖር ወሳኝ ቅድመ ሁኔታዎች ናቸው።
በፖለቲካል ሳይንስ እና በዓለም አቀፍ ግንኙነት ምሁራን ዘንድ እንደሚታመነው የአንድ ሀገር የውጭ ፖሊሲ እና የዲፕሎማሲ አቅም የውስጥ ፖለቲካዊ ቁመናዋ ቀጥተኛ ነጸብራቅ ነው። በሪያሊዝም ዕይታ መሠረት አንዲት ሀገር ብሔራዊ ጥቅሟን በዓለም አቀፍ መድረክ ማስከበር የምትችለው የውስጥ ደኅንነቷን እና አቅሟን ስታጠናክር ብቻ ነው።
የኢትዮጵያ የሥልጣን ሽግግሮች እና የፖለቲካ ማኅበረሰብ ግንባታ ሂደቶች በአብዛኛው በኅይል፣ በመጠላለፍ እና “አሸናፊው ሁሉንም ይወስዳል፤ ተሸናፊው ሁሉንም ያጣል” በሚለው የዜሮ-ድምር የፖለቲካ መርህ ላይ ነበሩ። በዘመነ መሳፍንት ወቅት የነበረው የውስጥ መከፋፈል ሀገሪቱ ጠንካራ እንዳትኾን አድርጓታል። በቅርብ ታሪካችንም ከአጼዎቹ ዘመን ወደ ደርግ፣ ከደርግም ወደ ኢህአዴግ የተደረጉት ሽግግሮች በጠመንጃ አፈሙዝ የተፈጸሙ ናቸው። ይህ ታሪካዊ የታፈነ ቅሬታ እና ያልተፈታ የጋራ ትርክት እጦት ሀገሪቱ የውስጥ ሰላሟን እንዳታረጋግጥ እና የውጭ ኅይሎች የውስጥ ክፍተትን ተጠቅመው በጣልቃ ገብነት ብሔራዊ ጥቅሟን እንዲፈታተኑ ሰፊ በር ከፍቶ ቆይቷል።
ጣሊያን የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለመድፈር ባሰፈሰፈችበት የፈተና ዘመን ዳግማዊ አጼ ምኒሊክ ያስተጋቡት የዓድዋ የክተት አዋጅ የውስጥ አንድነት ለሀገር ህልውና ያለውን ወሳኝ ትርጉም ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ነው። ንጉሠ ነገሥቱ በየአካባቢው ያሉ አለመግባባቶች፣ የሥልጣን ሽኩቻዎች እና የእርስ በርስ መናቆሮች ለጠላት ትልቅ ክፍተት እንደሚፈጥሩ እና ኢትዮጵያዊ ማንነትን ለማጥፋት ብርቱ ጉልበት እንደሚኾኑ ቀድመው ተገንዝበው ነበር።
በመኾኑም መላው ሕዝብ እና የየአካባቢው መሪዎች የግልም ኾነ የጎሳ ልዩነቶቻቸውን ወደ ጎን ትተው ለሀገር ነጻነት በአንድነት እንዲቆሙ “አመልህን በጉያህ…” ጥሪን አቅርበዋል።
ትላንትና ሉዓላዊነትን ያስጠበቀው የአጼ ምኒሊክ ታሪካዊ ንግግር ዛሬም ለሀገራችን ወቅታዊ መልዕክት አለው። የውስጥ ልዩነቶች፣ አለመግባባቶች እና መከፋፈሎች ለብሔራዊ ደኅንነት ስጋት እንዳይኾኑ እና ለውጭ ጣልቃ ገብነት ስንጥቃት እንዳይፈጥሩ ችግሮችን በጠረጴዛ ዙሪያ ፈትቶ ጠንካራ ሀገርን ለመገንባት ሀገራዊ ምክክሩ እጅግ ወሳኝ ኾኖ ይነሳል።
ምክክሩ የግጭት እና የፀብ አጫሪ አዙሪትን በመስበር ወደ አዎንታዊ ድምር ፖለቲካ ማሻገርን ዓላማው ያደረገ ነው። ሀገራዊ ምክክሩ በስኬት ከተጠናቀቀ ለብሔራዊ ጥቅም መከበር የሚያበረክተው ትልቁ አስተዋጽኦ የውስጥ አንድነትን እና የማይበገር አቅምን መፍጠር ነው።
በምክክሩ አማካኝነት ዘመናትን የተሻገሩ ታሪካዊ ቁርሾዎች፣ የማንነት እና የሀብት ክፍፍል ጥያቄዎች፣ የፖለቲካ ሥልጣን ውድድሮች በጠረጴዛ ዙሪያ ከተፈቱ ኢትዮጵያ የውስጥ ተጋላጭነቷን በእጅጉ ትቀንሳለች።
ጠንካራ የውስጥ አንድነት ያላት ሀገር ደግሞ በጂኦ-ፖለቲካዊ መድረክ በተለይም እንደ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ባሉ የውኃ ላይ ድርድሮች፣ በቀይ ባሕር ቀጣና ፖለቲካ እና ከዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በሚኖራት ግንኙነት አንገቷን ቀና አድርጋ ብሔራዊ ጥቅሟን ማስከበር ትችላለች።
ስኬታማ የሰላም ግንባታ ሂደት ሀገሪቱ በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ዘንድ ያላትን አመኔታ በእጅጉ በመጨመር ተሰሚነቷ እና ተደማጭነቷ እንዲያድግ ያደርጋል።
ምክክሩ የሀገሪቱን የኢኮኖሚ እና ዲፕሎማሲያዊ አቅም ይበልጥ ለማሳደግም ትልቅ ጉልበት ይኖረዋል። ዘላቂ ሰላም እና መግባባት ከሌለ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት መሳብ፣ ቱሪዝምን ማሳደግም ኾነ የዜጎችን ኑሮ ማሻሻል አይቻልም። የልማት ኢኮኖሚክስ ምሁሩ ፖል ኮሊየር እ.ኤ.አ. በ2007 ባሳተሙት ‘ዘ ቦተም ቢሊየን’ በተሰኘው መጽሐፋቸው እና ተያያዥ ጥናቶቻቸው ሀገራት በግጭት አዙሪት ውስጥ ሲወድቁ አንጡራ ሀብታቸው ይወድማል፤ ከድህነት ለመውጣትም ይቸገራሉ። የኖቤል ተሸላሚው ዳሮን አሴሞግሉ እና ጀምስ ሮቢንሰን በበኩላቸው ሁሉን አሳታፊ ያልኾኑ የፖለቲካ ሥርዓቶች ለግጭት እና ለኢኮኖሚ ውድቀት እንደሚዳርጉ አረጋግጠዋል።
ሀገራዊ ምክክሩ ተደጋጋሚ የግጭት አዙሪትን በመስበር የሀገሪቱን ሀብት እና ውድ የሰው ኅይል ከእርስ በርስ ግጭት ወደ ልማት እንዲዞር የማድረግ ከፍተኛ ኅይልም አለው። ይህ ደግሞ በራሷ የምትተማመን እና ጠንካራ ኢኮኖሚ ያላት ሀገር እንድትፈጠር በማድረግ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም በጠንካራ መሠረት ላይ ለማቆም ያግዛል።
ኢትዮጵያ ከታሪኳ ተምራ ዜጎች ከመንግሥት ጋር ያላቸውን ግንኙነት የሚያድስ አዲስ ማኅበራዊ ውል በመፈጸም እና ዜጎቿን በእኩልነት የምታስተናግድበትን ጠንካራ መሠረት እንድትጥል ሁሉም ለምክክሩ አወንታዊ ውጤት የበኩሉን ሊወጣ ይገባል።
ዘጋቢ:- ስማቸው አጥናፍ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleየኢልኒኖ ስጋት እስከ ምን?
Next articleየምሥራቅ ዕዝ ሬጅመንት በወንበርማ ወረዳ ከሕዝቡ ጋር በመቀናጀት የመንገድ ጥገና በጎ አድራጎት ሥራዎችን አከናወነ።