የኢልኒኖ ስጋት እስከ ምን?

6
ባሕር ዳር: ሐምሌ 21/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በዓለም ሜቲዮሮሎጂ ድርጅት መረጃ መሠረት በፓሲፊክ ውቅያኖስ ላይ በፍጥነት በማደግ ላይ ያለው የኤልኒኖ (El Niño) ክስተት በዓለም አቀፍ የዝናብ ሥርጭት ላይ መሠረታዊ እና ከፍተኛ ለውጥ እያስከተለ ይገኛል።
የፓሲፊክ ውቅያኖስ ውኃ ከተለመደው በላይ መሞቅ በተለይ በምሥራቅ አፍሪካ የዝናብ ደመናዎችን በመገታት ቀጠናውን ለድርቅ እና ለምግብ ዋስትና ሥጋት ማጋለጡን የዓለም ሜቲዮሮሎጂ ድርጅት ሳይንሳዊ ዳሰሳ ያመላክታል።
ይህ የአየር ንብረት መዛባት በተያዘው የክረምት ወቅት በአንዳንድ የዓለም ክፍሎች ከመደበኛው በላይ የኾነ ከፍተኛ ዝናብ እና የጎርፍ አደጋ የሚያስከትል ሲኾን በሌሎች ክፍሎች ደግሞ የድርቅ እና የዝናብ እጥረት ሥጋትን ደቅኗል።
በዚህ መሰረት፦
#ማዕከላዊ እና የምሥራቃዊ ኢኳቶሪያል እና የደቡባዊ አፍሪካ ክፍሎች ከመደበኛው በላይ ዝናብ የሚጠበቅባቸው አካባቢዎች ናቸው።
#ከመደበኛው ያነሰ (ዝቅተኛ) ዝናብ የሚጠበቅባቸው አካባቢዎች ተብለው ከተለዩት ውስጥ ደግሞ ምሥራቅ አፍሪካ አንዱ ነው።
በምሥራቅ አፍሪካ በሚገኘው የአፍሪካ ቀንድ አካባቢ የኤልኒኖ መከሰት የዝናብ ደመናዎችን እንቅስቃሴ ስለሚገታው የክረምት ዝናብ መጠን ከመደበኛው ያነሰ እያደረገው ነው። ኢትዮጵያም አንዷ የዚህ ክስተት ተጋላጭ ናት።
የኢትዮጵያ ሜትሮሎጂ ኢንስትቲዩትም ከሰኔ 2018 ዓ.ም እስከ መስከረም 2019 ዓ.ም ያለውን ትንበያ አስቀምጧል።
በዚህም ዋነኛ የክረምት ዝናብ ተጠቃሚ በኾኑ የሰሜን ምሥራቅ እና የምሥራቅ የሀገሪቱ አካባቢዎች ላይ “መደበኛ እና ከመደበኛ በታች ያመዘነ” እንዲኹም በመካከለኛው እና በሰሜን ምዕራብ “መደበኛ እና ከመደበኛ በታች” ዝናብ ይኖራል።
በክረምቱ መግቢያ እና በመውጫው የመስከረም ወር የዝናብ ሥርጭት “የተዛባ እና ደረቅ ሰሞናት የሚዘወተርበት” እንደሚኾን አስቀምጧል።
የዝናብ እጥረት ጫናውም በግብርና፣ በውሃ አቅርቦት፣ በምግብ ደኅንነት እና በኅብረተሰብ ጤና ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድር እንደሚችል ተገልጿል።
ጥንቃቄውስ?
#የቅድመ ማስጠንቀቂያ መረጃዎችን እስከ ታች ማኅበረሰቡ ድረስ በማድረስ ቅድመ ዝግጅት እንዲኖር ማድረግ
#አልፎ አልፎ በጎርፍ ተጋላጭ በኾኑ አካባቢዎች የመልሶ ማቋቋም እና የፍሳሽ ማስወገጃ ሥራዎችን ማዘጋጀት፤
#በድርቅ ተጋላጭ በኾኑ አካባቢዎች ደግሞ የውኃ አማራጮችን ማዘጋጀት እና ድቅል እና ቶሎ የሚደርሱ ዘሮችን ማቅረብ
#የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር አካላት፣ የግብርና ተቋማት እና የበጎ አድራጎት ድርጅቶች የጋራ የመጠባበቂያ እቅድ በማዘጋጀት ፈጣን ምላሽ ለመስጠት መዘጋጀት ይጠበቅባቸዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleየፖሊስ ተቋምን በሰው ኀይል እና በቴክኖሎጂ የዳበረ ለማድረግ በትኩረት እየተሠራ ነው።
Next articleሀገራዊ ምክክሩ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም መከበር ምን አበርክቶ ይኖረዋል?