የፖሊስ ተቋምን በሰው ኀይል እና በቴክኖሎጂ የዳበረ ለማድረግ በትኩረት እየተሠራ ነው።

5

 

የኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ፖሊስ መምሪያ የ2018 በጀት ዓመት የሥራ አፈጻጸም ግምገማ በከሚሴ ከተማ አካሂዷል።

በመርሐግብሩ የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ኮሚሽነር ጄኔራል ዘላለም መንግሥቴ (ዶ.ር)፣ የኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ዋና አሥተዳዳሪ አህመድ አሊን ጨምሮ የብሔረሰብ አሥተዳደሩ፣ የክልሉ ፖሊስ አዛዦች እና አባላት ተሳትፈዋል።

የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ኮሚሽነር ጄኔራል ዘላለም መንግሥቴ (ዶ.ር) በብሔረሰብ አሥተዳደሩ አሁን ለተስተዋለው ሰላም የፖሊስ አባላቱ እና አዛዦች ሚና ከፍተኛ መኾኑን ተናግረዋል።

የፖሊስ ተቋም ነፃ እና ገለልተኛ እንዲኾን፣ ዓለማቀፋዊ ባሕሪ እንዲኖረው ለማስቻል በርካታ የሪፎርም ሥራ ሢሠራ መቆየቱን ጠቅሰዋል። በዚህም በርካታ ስኬቶች ተመዝግበዋል ብለዋል።

የፖሊስ ተቋምን በሰው ኀይል እና በቴክኖሎጂ የዳበረ እንዲኾን ለማስቻልም በትኩረት እየተሠራ መኾኑን አስረድተዋል።

የወንጀል መከላከል ሥራዎች በቴክኖሎጂ እንዲደገፉ በማስቻል ከአንድ ቦታ መቆጣጠር የሚችል ተቋም እየተገነባ ነው ብለዋል።

የኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ዋና አሥተዳዳሪ አህመድ አሊ ብሔረሰብ አሥተዳደሩ በሠራው የተቀናጀ የሰላም ግንባታ ሥራ አሁን ላይ ማኅበረሰቡ በሰላም ወጥቶ እንዲገባ ማድረግ መቻሉን ገልጸዋል።

በብሔረሰብ አሥተዳደሩ ሰላም እንዲሰፍን ለማስቻል በተሠራው ሥራ የፖሊስ አባላት እና አዛዦች ሚና ከፍተኛ መኾኑንም አስረድተዋል።

የጸጥታ ተቋማትን የመፈፀም አቅም ለማሳደግ በጸጥታ መዋቅሩ የአቅም ግንባታ ሥልጠናዎች እንዲመቻቹ ይሠራልም ብለዋል።

የኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ፖሊስ መምሪያ አዛዥ ዋና ኢንስፔክተር ኡመር መሀመድ የብሔረሰብ አሥተዳደሩ ፖሊስ ከሌሎች የጸጥታ መዋቅር ጋር በመቀናጀት በሠራው የሕግ ማስከበር ሥራ በርካታ ስኬቶች መመዝገባቸውን ጠቅሰዋል።

ሌሎች የፖሊስ መሪዎችም በ2018 በጀት ዓመት በብሔረሰብ አሥተዳደሩ ሰላም እንዲሰፍን በወንጀል መከላከል፣ ሕገወጥ የመሳሪያ እና የሰዎች ዝውውርን ለማስቀረት በርካታ ሥራዎችን ሢሠሩ መቆየታቸውን አብራርተዋል።

ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎቹ የልማት ሥራዎችን ጎብኝተዋል። የችግኝ ተከላ መርሐ ግብርም አካሂደዋል።

#አሚኮ #AmharaPolice

#ከሚሴ #ሐምሌ_20_2018_ዓ_ም

ዘጋቢ:-ይማም ኢብራሒም

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous articleየመከሩ በሰላም ብዕር እና ብራና የተጻፈ ታሪክ ለልጆቻቸው አስረክበዋል።