
ሀገርን የሚያጸናው ሰላም፣ ፍቅር እና ምክክር ነው። ጸብ እና ጦርነት ሀገርን ያሳንሳል፤ ሕዝብን ለስቃይ ይዳርጋል። ለጠላትም አሳልፎ ይሰጣል።
ምክክር ውስጣዊ አንድነትን ያጠነክራል፤ ነጻነትን ያጸናል፣ ሉዓላዊነትን ያስጠብቃል። መመካከር ጠላቶች የሚገቡባቸው ክፍተቶች እንዳይኖሩ ያደርጋል።
የመከሩ በሰላም ብዕር፣ በሰላም ብራና የተጻፈ ታሪክ ለልጆቻቸው አስረክበዋል፤ ሰላማዊት ሀገርን ከእነ ክብሯ ለልጆቻቸው ሰጥተዋል።
በወንድማማቾች መካከል ፍቅር እንጂ ጦርነት፣ አንድነት እንጂ መለያያት፣ መደጋገፍ እንጂ መጠላለፍ አያስፈልግም። ሀገር የምትኮራው ከጠላቶቿ በላይ ኾና የምትኖረው ልጆቿ በአንድነት ሲጸኑላት፣ በፍቅር ሲኖሩላት፣ ሰላም እና አብሮነትን ሲያዳብሩላት ነው።
ኢትዮጵያውያን ችግሮቻቸውን በምክክር ፈትተው ሰላምን ሊያጸኑ፣ ሀገረ መንግሥት ግንባታቸውን ሊያጠናክሩ በአንድ ጣሪያ ሥር ተሠባሥበው እየመከሩ ነው። በዚህ ምክክር ኢትዮጵያ በልጆቿ ተደስታለች፤ ተስፋንም ሰንቃለች።
በባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ ምሁራን የተሠራው እና በኢትዮጵያ ማኅበራዊ ሳይንስ ጆርናል የወጣው “የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር፡ ዘላቂ ሰላምን እና የሀገር ግንባታን ለማረጋገጥ ያለው እምቅ አቅም እና ፈተናዎቹ” በሚለው ጥናታዊ ጽሑፍ ምክክር የግንኙነቶች መሠረት የኾነ ልዩ የመገናኛ ዘዴ ነው፤ ልዩነቶችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት እና ለዴሞክራሲያዊ አሠራር ትልቅ አስተዋጽኦ አለው ተብሎ ተመዝግቧል።
ምክክር የሚደረገው መረዳዳትን፣ ትብብርን እና አዎንታዊ ግንኙነቶችን ለመገንባት ነው። ምክክር ሰዎች በግልጽ የሚነጋገሩበት፣ እርስ በእርስ በመከባበር መንገድ እና በትኩረት የሚደማመጡበት ነው ይላል።
ምክክር ማጥቃትን እና መከላከልን ያስወግዳል፤ የሌሎችን ፍላጎት፣ ዓላማ ወይም ስብዕና በሚመለከቱ ግምቶች ላይ ተመስርተው የሚሰጡ አቋራጭ እና አዋራጅ ድምዳሜዎችን ይከለክላል ነው የሚለው።
ሀገራዊ ምክክር በከፍተኛ የፖለቲካ ቀውስ፣ ከጦርነት በኋላ ባሉ ሁኔታዎች ወይም ሰፊ በኾኑ የፖለቲካ ሽግግሮች ወቅት በብዙ ቁጥር ባላቸው የሀገር ውስጥ ባለድርሻ አካላት መካከል ስምምነትን ለመፍጠር የሚደረግ፣ በሀገር በቀል ባለቤትነት የሚመራ ሂደት ነው።
ሀገራዊ ምክክር ለግጭት አፈታት እና የፖለቲካ ለውጦችን ለማሥተዳደር ከጊዜ ወደ ጊዜ ተወዳጅነቱ እየጨመረ የመጣ መሳሪያ ነው ይላል። ስለ ሀገሪቱ የወደፊት አቅጣጫ የሚደረጉ ክርክሮችን ከተለመዱት የፖለቲካ ልሂቃን ውሳኔ ሰጭነት አሻግሮ ሌሎች እንዲሳተፉበት የሚያደርግ ተግባር ነው።
ምክክር በግጭት ውስጥ ባሉ የፖለቲካ ኀይሎች መካከል መግባባትን ለመፍጠር፣ ዋና ዋና የፖለቲካ ልዩነቶችን ለመፍታት እና የአመጻ እንቅስቃሴዎችን ለማራቅ ከሚያገለግሉ መሳሪያዎች መካከል አንዱ ነው። የፖለቲካ ቀውሶችን ለመፍታት፣ ለፖለቲካዊ ሽግግሮች እና ለዘላቂ ሰላም መንገድ ለመክፈት የሚያገለግል ነው ይላል ጥናቱ።
ሀገራዊ ምክክር በሀገር አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ትኩረት ለሚሹ ቀውሶች ምላሽ ለመስጠት፣ በመንግሥት እና በኅብረተሰቡ መካከል አዲስ የማኅበራዊ ውል ለማሰር ይደረጋል የሚለው ጥናቱ ሀገራዊ ምክክር ተሳተፎን እና አካታችነትን የሚያረጋግጥ ነው።
ሀገራዊ ምክክር አብዛኛውን ጊዜ ከፖለቲካ ድርድሮች የተገለሉ ወይም ዝቅተኛ ውክልና ያላቸው ወገኖች እና ቡድኖች ዕድል እንዲያገኙ ያደርጋል። በዚህም ምክንያት ምላሽ ያላገኙ ጥያቄዎችን በግልጽ ለማንሳት ያስችላል።
ሀገራዊ ምክክር ለኢትዮጵያ የሰላም ግንባታ ወሳኝ መድረክ ነው። ግጭቶችን ወደ ሰላማዊ መንገድ በመቀየር የበለጠ የተስማማ ማኅበረሰብ እንዲፈጠር ያደርጋልና ነው የሚለው።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ የረጅም እና የአጭር ጊዜ ውጣ ውረዶችን ለመፍታት ተግባራዊ መፍትሔ ነው። ይህ አካሄድ ተደጋጋሚ የኾኑ የኀይል ግጭቶችን በማስቆም፣ መሠረታዊ መብቶች እና ነጻነቶችን በመመለስ የሰላም ግንባታ ሂደቱን ያጠናክራል።
ሰብአዊ ቀውስን ለማቃለል፣ እርቅን ለማስፋፋት እና የፖለቲካ ውጥረቶችን በመሻገር ሰላምን ለማስፈን ያስችላል። የኢትዮጵያን አጣብቂኝ ግጭቶች ለመፍታት እና ዘላቂ የሰላም ግንባታ ማዕቀፍ ለመገንባት፣ ሀገራዊ የምክክር ሂደትን ማካሄድ እጅግ አስፈላጊ ነው የሚለው ጥናቱ ይህ ሂደት የማኅበራዊ ትስስርን፣ አሳታፊ የኾነ አሥተዳደርን እና ዘላቂ ልማትን ለማስፋፋት ዕድል ይሰጣል ነው የሚለው።
በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለው ሀገራዊ ምክክር አካታችነትን ለማስፈን፣ መሠረታዊ የኾኑ ሰብዓዊ እና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን ለማስከበር እና በሀገሪቱ ውስጥ መዋቅራዊ ማስተካከያዎችን ለማድረግ ያስችላል።
ምክክሩ ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ እሴቶቿን ለማጠናከር እና ሀገራዊ ማንነቷን ለማጎልበት ያደረገችው ወሳኝ እርምጃ ነው የሚለው ጥናቱ ውይይቱ የሁሉም ዜጎች ድምጽ የሚሰማበት እና መብቶቻቸው የሚከበሩበትን ዕድል የፈጠረ ነው ይላል።
ምክክር ወካይ እና የጋራ ምልክት የኾኑ ተቋማትን ለመገንባት የሚያስችል፣ ከፉክክር እና ውጊያ ይልቅ የጋራ ነገ እና የጋራ ራዕይ ላላት ሀገር ትልቅ ዕድል የሚሰጥ ነው። ኢትዮጵያ በምክክር ለማኅበራዊ ትስስር ቅድሚያ በመስጠት የላቀ አንድነትን መገንባት እና በሕዝቦቿ መካከል ሰላማዊ አኗኗርን ማጎልበት ትችላለች።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ሂደት ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ ለብዙ ኢትዮጵያውያን ትልቅ ተስፋን ሰጥቷል። የምክክሩ መጀመር ምስቅልቅል ለኾኑ ችግሮች መፍትሔ ይዞ እንደሚመጣ ይጠበቃል።
በምክክሩ ሀገር አጽኑ፤ የሀገርን ሰላም እና ተስፋም ገንቡ።
በታርቆ ክንዴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
