
ተማሪ ተመሥገን ሉሌ በደብረ ታቦር ከተማ የ2018 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ መልቀቂያ ፈተናን ከወሰዱ ተማሪዎች መካከል አንዱ ነው። ይህ ባለብሩህ አዕምሮ ተማሪ በፈተናው 579 ነጥብ 99 በማምጣት ከፍተኛ ውጤት አስመዝግቧል።
በውጤቱ መሠረት በሀገር አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ውጤት ካስመዘገቡ ተርታ ሲመደብ፥ በዞኑ ደግሞ አንደኛ ደረጃን መያዝ እንደቻለ ተናግሯል።
ክረምቱን ገጠር ቤተሰቦቹን በግብርና ሥራ እያገዘ በማሳለፍ ላይ የሚገኘው ይህ ጎበዝ ተማሪ ውጤት የመለቀቁን ጭምጭምታ ሲሰማ የኾነውን ሲያስረዳ “ውጤት እንደተለቀቀ ስሰማ ኔትወርክ የሚሠራበት ተራራ ላይ ወጥቼ ከተማ ለሚገኘው ወንድሜ ደውዬ ውጤቴን እንዲያይልኝ ነገርኩት። ከዚያም ውጤቴን ሲነግረኝ ከነበርኩበት ተራራ ላይ ሆኜ በደስታ አልቅሻለሁ” ብሏል።
👨ተማሪው የወላጆች ኩራት መኾን ወላጅ አባቱ አቶ ሉሌ ተኮላ በልጃቸው ሙሉ መተማመን እንደነበራቸው በኩራት ገልጸዋል። “በትምህርቱ ውጤታማ እንደሚኾን ቀድመን ስለተረዳን ከተማ አስገብተን በግል ትምህርት ቤት እንዲማር አድርገነዋል። ልጃችንም አላሳፈረንም። ባስመዘገበው ከፍተኛ ውጤትም እጅጉን ኮርተናል፤ ይገበዋልም። ልጄ የምንተማመንበት የሀገር ኩራት ነው” ብለዋል።
ወደፊትም በልጃችን ሙሉ በሙሉ እንተማመናለን የሚሉት አቶ ሉሌ የመንግሥትን ድጋፍ ካገኘ ከእኛ አልፎ ለሀገር ጠቃሚ እና አስፈላጊ ሰው እንደሚኾን አልጠራጠርም ነው ያሉት።

ዘጋቢ፦ አድኖ ማርቆስ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
