587 ያመጣው የኮከቡ ተማሪ ሙባረክ የስኬት መንገድ

84
🎉🎉
ተማሪ ሙባረክ መሐመድ የይሁኔ ወልዱ መታሰቢያ ደሴ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት ተማሪ ነው። በ2018 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ሀገር ዓቀፍ ፈተና ከ600 ጥያቄ 587 በመመለስ ከፍተኛ ውጤት ካስመዘገቡት መካከል መኾን ችሏል ።🌟
✨ የተማሪው የቀደመ ታሪክ ! ተማሪ ሙባረክ እንደተናገረው የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን በታች አርማጭሆ ወረዳ ሳንጃ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ተምሯል። ቀጥሎም ከ9ኛ ክፍል ጀምሮ በይሁኔ ወልዱ መታሰቢያ ደሴ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት ሲከታተል ቆይቷል።
🥇በተለይም ከ10ኛ ክፍል ጀምሮ በትምህርት ቤቱ ከፍተኛውን ውጤት እያስመዘገበ የአንደኛ ደረጃን እየያዘ ቀጥሎ በ12ኛ ክፍል ማጠናቀቂያ ፈተና የላቀ ውጤት አምጥቷል።
✨ የስኬታማነቱ ሚስጥር💡
ለዚህ ስኬታማነቱ በክፍል ውስጥ መምህራን የሚያስተምሩትን ትምህርት በንቃት በመከታተል፤ በክፍል ውስጥ የተማረውን በየቀኑ መከለስ እና አብዛኛውን ጊዜውን በንባብ ማሳለፉ መኾኑን ገልጿል።
በተለይም ከ9ኛ እስከ 12ኛ ክፍል ያሉትን የትምህርት አይነቶች ጭምር እያጠና ለፈተና መዘጋጀቱ ለ12ኛ ክፍል ውጤቱ አንዳገዘው የትጋት መንገዱን አስረድቷል።
📖“ለጥናት ስልት የተፈጥሮ መንገድን እከተላለሁ” የሚለው ተማሪ ሙባረክ “ቀን በደንብ ሙሉ ጊዜዬን ለንባብ አውላለሁ፤ ማታ ደግሞ በቂ እንቅልፍ አገኛለሁ ይህም ለተሻለ መረዳት ያግዛል” ብሏል። በዚህም ለስኬት መብቃቱን ነው የገለጸው።
✨ የትምህርት ቤቱ እና የመምህራን ድጋፍለተማሪ ሙባረክ ስኬት የትምህርት ቤቱ መምህራን ከፍተኛ ድርሻ እንዳላቸው ተናግሯል። “ውጤቱ የእኔ ብቻ ሳይኾን የመምህራን ጭምር ነው ምክንያቱም በእያንዳንዷ የትምህርት ሂደት የመምህራን ሚና ከፍተኛ ነው”ብሏል።
የትምህርት ቤቱ ርእሰ መምህር ሳሊም አሕመድ ፤ ሙባረክ መልካም ስነ ምግባር ያለው፣ ትጉህ እና ታታሪ እንደኾነ ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል።
የጥናት መርሐ ግብር በሚመቸው መንገድ ራሱ አዘጋጅቶ የሚመራ፣ በእርስ በርስ መረዳዳት ግንባር ቀደም፣ በትምህርት ቤቱ አርዓያ የኾነ እና ትልቅ ርዕይ ያለው ተማሪ ነው ብለዋል።
🎉 የወላጅ ድጋፍ እና ደስታ ! የተማሪ ሙባረክ ወላጅ አባት ሙሐመድ አየነው ልጃቸው ከበፊት ጀምሮ በጥሩ ሥነ ምግባር ያደገ መኾኑን አንስተዋል። ለትምህርቱ ልዩ ፍቅር ስላለው ውጤታማ እንዲኾንም እንደወላጅ የሚችሉትን ሁሉ ድጋፍ ማድረጋቸውን ጠቁመዋል።
አኹን ላይ ከፍተኛ ውጤት ማምጣት በመቻሉም ከፍተኛ ደስታ እንደተሰማቸው ገልጸዋል።
💡 የተማሪው የወደፊት ርዕይ ተማሪ ሙባረክ ለወደፊት በሜካኒካል ኢንጅነሪንግ ዘርፍ ማጥናት እንደሚፈልግ ተናግሯል። ከልጅነቱ ጀምሮ የምወደው ዘርፍ በመኾኑ በኢንጅነሪንግ ዘርፎች መፍትሔ በሚያመጡ የቴክኖሎጂ ሥራዎች ላይ የራሱን አስተዋጽኦ ማበርከት እንደሚፈልግ ሀሳቡን አጋርቶናል።
✍️ዘጋቢ:- አሰፋ ልጥገበው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleበዓል በመጣ ቁጥር ሕዝብን የሚያማርረው የትራንስፖርት ችግር!
Next article” ውጤቴን ስሰማ በደስታ አልቅሻለሁ” የከፍተኛ ውጤት ባለቤቱ ተመሥገን ሉሌ