በዓል በመጣ ቁጥር ሕዝብን የሚያማርረው የትራንስፖርት ችግር!

29
ከታሪፍ በላይ የሚደረግ ክፍያ እያማረራቸው መኾኑን ነዋሪዎች ሲገልጹ፤ የክልሉ መንገድ ትራንስፖርት እና ሎጅስቲክስ ቢሮ ደግሞ የችግሩን መኖር አምኖ ለእርምት እየሠራ ነው።
በተደጋጋሚ ከጎንደር ወደ ገንዳ ውኃ ጉዟቸውን የሚያደርጉ ነዋሪዎች ከታሪፍ በላይ የሚደረግ ክፍያ እና በትርፍ የመጫን ተግባር ከፍተኛ ጫና እያደረሰባቸው መኾኑን ለአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ተናግረዋል።
ከ150 ኪሎ ሜትር በታች ለኾነ መንገድ በተሽከርካሪዎች ደረጃ መጠን እስከ 500 ብር ታሪፍ እንደወጣለት ያነሱት ነዋሪዎቹ በሕገ ወጥ ታሪፍ ጭማሪ እስከ 1 ሺህ 500 ብር እየከፈሉ መኾኑን ገልጸዋል።
በመናኽሪያ ውስጥ በኢ_ትኬት በትክክለኛ ታሪፍ ቢከፍሉም “ነዳጅ ጨምሯል፤ መንገድ ላይ ለተለያዩ አካላት እንከፍላለን” በሚሉ ምክንያቶች ዋጋ እንደሚጨመርባቸው አንስተዋል።
በትራንስፖርት ምክንያት በሸቀጦች ላይ የዋጋ ጭማሪ እንዲኖር፤ የኑሮ ውድነት እንዲከሰት፤ ሰው ሕመም ሲገጥመው በትራንስፖርት ተጉዞ ሕክምና ማግኘት እንዳይችል ፈተና ኾኗል ነው ያሉት። በበዓላት ወቅት ችግሩ ይበልጥ እንደሚጎላም ተናግረዋል።
ከታሪፍ በላይ መከፈሉን በሚያጋልጡ አንዳንድ ነዋሪዎች ላይ ደግሞ የማዋከብ እና ሌሎች ተሳፊሪዎችም ውሸት ነው ብለው የመሸፈን ተግባር እንደሚፈጽሙ ነው የገለጹት። የትራንስፖርት ተቆጣጣሪዎች ሕዝብ ሲያጋልጥ አሽከርካሪዎችን የመቅጣት፤ ያለ አግባብ የተከፈለ ክፍያን የማስመለስ፤ ተሽከርካሪዎችን የማሰር እና ሌሎች እርምጃዎችን እየወሰዱ መኾኑን መታዘባቸውን ገልጸዋል።
ኅብረተሰቡ ከታሪፍ በላይ የሚደረግን ክፍያ በማጋለጥ መብቱን ሊያስከብር ይገባል ነው ያሉት።
የአማራ ክልል መንገድ፤ ትራንስፖርት እና ሎጅስቲክስ ቢሮ ችግሩን ለመቅረፍ ምን ሠራ?
ቢሮው ችግሮችን በየጊዜው በመገምገም ለመቅረፍ እየሠራ መኾኑን የትራንስፖርት አገልግሎት አቅርቦት ብቃት ማረጋገጫ ስምሪት ዳይሬክተር ጌታቸው መርሻ ተናግረዋል። በ104 መናኽሪያዎች በቅድመ ትኬት አገልግሎት (ኢ_ትኬቲንግ) በዲጂታል የታገዘ አገልግሎት እየተሠጠ ነው ብለዋል።
የቅድመ ትኬት አገልግሎት ምን ውጤት አመጣ?
የአገልግሎት ተጠቃሚዎች ከአሽከርካሪዎች እና ከረዳቶች ጋር ሳይገናኙ በቀጥታ ኢ_ትኬት ላይ እንዲቆርጡ ተደርጓል። ይህም ከታሪፍ በላይ ክፍያ እና ትርፍ የመጫን ተግባር በመናኽሪያ ውስጥ ማስቀረት ችሏል ነው ያሉት። ከመናኽሪያ ውጭ ከታሪፍ በላይ እንዲጨምሩ የማድረግ እና ትርፍ የመጫን ተግባር ግን እየተፈጸመ እንደሚገኝ አንስተዋል።
👉 ምን እርምጃ ተወሰደ?
ኅብረተሰቡ በሚሰጠው ጥቆማ መሠረት ከገንዘብ ቅጣት እስከ ስምሪት ማገድ እርምጃ እየተወሰደ ነው ብለዋል። በመንገድ ላይ የሚገኙ ደንብ ተቆጣጣሪዎች ጠንካራ ሕግ የማስከበር ተግባርን እየፈጸሙ መኾናቸውን ተናግረዋል።
የሕግ ጥሰትን በአብዛኛው መቀነስ መቻሉን ያነሱት ዳይሬክተሩ ለተቆጣጣሪዎች ምቹ ባልኾኑ አካባቢዎች ላይ ግን ተግባሩ መቀጠሉን ተናግረዋል። በቀጣይም የበዓል ወቅትን ጨምሮ የሚፈጸሙ ከታሪፍ በላይ ክፍያዎችን ለማስቆም ሕግ የማስከበር ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት።
👩‍👩‍👧‍👦 ከማኅበረሰቡ ምን ይጠበቃል?
መንግሥት በወጭ ላይ የተመሠረተ ታሪፍ ያስቀመጠ በመኾኑ አሽከርካሪዎች ሕግን ማክበር አለባቸው ብለዋል። በየመንገዱ ለሚገኙ የሕግ አስከባሪዎች በማሳወቅ እና በየመናኽሪያው የተቀመጡ ነጻ የስልክ መሥመሮች ላይ ሕገ ወጥ ተግባርን ደውሎ በማጋለጥ ከታሪፍ በላይ ክፍያን ለማስቆም ማኅበረሰቡ መብቱን እንዲያስከብር አሳስበዋል።
ዘጋቢ:- ያየህ ፈንቴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleየመድኃኒት አቅርቦትን ወደ ዲጂታል ሥርዓት በማሸጋገር ውጤታማ ሥራዎች ተሠርተዋል።
Next article587 ያመጣው የኮከቡ ተማሪ ሙባረክ የስኬት መንገድ