የመድኃኒት አቅርቦትን ወደ ዲጂታል ሥርዓት በማሸጋገር ውጤታማ ሥራዎች ተሠርተዋል።

13
በአዲስ አበባ ሲካሄድ የሠነበተው 76ኛው የዓለም ጤና ድርጅት የአፍሪካ ቀጣናዊ ኮሚቴ ሥብሠባ ተጠናቅቋል።
በጉባኤው የተሳተፉ የዓለም ጤና ድርጅት የአፍሪካ አባል ሀገራት ተወካይ እና የጤናው ዘርፍ ባለሙያዎች የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት እንዲሁም የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩትን ጎብኝተዋል።
የዓለም የጤና ድርጅት የአፍሪካ ቀጣና ባለሙያዎች የተቋሙን ሥራዎች እንዲሁም ኢትዮጵያ በጤናው ዘርፍ እያደረገች ያለችውን አሕጉራዊ ትብብር አድንቀዋል።
የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት ግቡን ለማሳካት የያዛቸውን ዕቅዶች እና የሥራ እንቅስቃሴውን አስመልክተው ሃሳቦችን አንስተዋል።
የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አብዱልቃድር ገልገሎ የመድኃኒት አቅርቦትን ወደ ዲጂታል ሥርዓት ማሸጋገር፣ የግዥ ሥርዓቱን ማዘመን፣ የክምችት፣ ሥርጭት አሠራርን ማስተካከል፣ የምርቶች አቅርቦት ሰንሰለት ቅንጅትን ማጠናከር እና ሌሎችንም የአገልግሎቱን የሪፎርም ሥራዎች አንስተዋል።
በዚህም የሀገር ውስጥ የመድኃኒት አቅርቦት በከፍተኛ ሁኔታ ማደጉን፣ በተለይም ቴክኖሎጂን በመጠቀም አጠቃላይ የግዥ እና የክምችት ሥርዓቱን በኤሌክትሮኒክስ መንገድ ማዘመን መቻሉን ገልጸዋል።
በ2030 እ.ኤ.አ በምሥራቅ አፍሪካ ፈጣን፣ ቀልጣፋ እና አስተማማኝ የመድኃኒት አቅርቦት ሰንሰለት ያለው ተቋም ለመኾን የሚያስችለውን የሦሥት ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅድ ቀርጾ እየተገበረ እንደሚገኝም ተጠቁሟል።
አገልግሎቱ በ5ኛው የአፍሪካ የአቅርቦት ሰንሰለት የልህቀት ሽልማት 2026 ከፍተኛውን የወርቅ ሽልማት ማሸነፉን እና ትልቅ ስኬት መኾኑም ተመላክቷል።
ዘጋቢ፦ መሠረት መቅጫ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleየኑሮ ውድነትን ለመቀነስ ተስፋ የተጣለበት ውህደት
Next articleበዓል በመጣ ቁጥር ሕዝብን የሚያማርረው የትራንስፖርት ችግር!