
በግብርናችን ውስጥ የትናንት ትልቁ ፈተና የአቅም ማነስ ብቻ አልነበረም። ይልቁንም የተበታተነ አቅምን አስተባብሮ ወደ ተሻለ ውጤት አለመቀየር እንጂ።
የአማራ ክልል የኅብረት ሥራ ማኅበራትን አደረጃጀት በመቀየር እና አቅማቸውን በማስተባበር ጠንካራ እና ተወዳዳሪ ተቋማትን ለመፍጠር በርካታ እርምጃዎችን በመውሰድ ላይ ይገኛል።
የዚህ አዲስ ምዕራፍ ሕያው ማሳያ የሚኾኑት ደግሞ በደቡብ ጎንደር ዞን የሚገኘው “የጉና” እና በምዕራብ ጎጃም ዞን የሚገኘው “የዕድገት ለአንድነት” የዘር ብዜት ግብይት እና ልማት የኅብረት ሥራ ዩኒየኖች ናቸው።
ሁለቱ ተቋማት የነበራቸውን አቅም፣ ልምድ እና ሀብት በማጣመር “አንድነት የዘር ብዜት እና ግብይት ዩኒዮን ኅብረት ሥራ ማኅበር” በሚል አዲስ መጠሪያ ታሪካዊ የውህደት ሥምምነት ፈጽመዋል።
ይህ ውህደት ለክልሉ አርሶ አደሮች፣ ሸማቾች እና አባላቱ ዘርፈ ብዙ ተጨባጭ ጥቅሞችን ይዞ መጥቷል፡
የአማራ ክልል ኅብረት ሥራ ማኅበራት ኮሚሽን ኮሚሽነር ጌትነት አማረ እንደገለጹት ውህደቱ የተበታተነ አቅምን ወደ አንድ ትልቅ የኢኮኖሚ ጉልበት የመቀየር እርምጃ ነው። ይህም ከምርጥ ዘር ብዜት ባሻገር ትላልቅ የልማት ፕሮጀክቶችን ለማካሄድ፣ ዘመናዊ የግብርና ማሽነሪዎችን ለመግዛት፣ ሰፊ የገበያ አማራጮችን ለመጠቀም እና ጠንካራ የፋይናንስ አቅምን ለመገንባት መንገድ ይከፍታል።
በየዕለቱ በአርሶ አደሮች እና በሸማቹ መካከል የሚቆሙ አላስፈላጊ ደላሎችን በማስወገድ እና ምርቶችን ከአምራቹ በቀጥታ በመረከብ ለሸማቹ ማቅረብ ያስችላል።
ይህም በምርት አቅርቦት እና በዋጋ ንረት ላይ የሚፈጠረውን ችግር ከመፍታት ባሻገር በሀገር ውስጥ እና በውጭ ገበያ ተወዳዳሪ ለመኾን ዕድል ይፈጥራል ነው ያሉት።
የአንድነት ኅብረት ሥራ ማኅበራት ዩኒየን ቦርድ ሠብሣቢ ደሴ ተረፈ እንደጠቆሙት ውህደቱ የሁለቱን ተቋማት የሰው ኀይል እና የቴክኖሎጂ አቅም በማጣመር ዘመናዊ አሠራርን በቀላሉ ለመተግበር ያስችላል።
በተለይም አርሶ አደሮች ጥራት ያለው የግብርና ግብዓት በወቅቱ እና በቅርበት እንዲያገኙ ያደርጋል።
በዕለቱ የተገኙት በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የገጠር ክላስተር አስተባባሪ ድረስ ሳህሉ (ዶ.ር) ባለፉት ዓመታት በክልሉ በበቆሎ ላይ ብቻ ተወሰኖ የነበረውን የምርጥ ዘር ብዜት አሁን ወደ ሌሎች የሰብል ዓይነቶች ማሳደግ አስፈላጊ ነው ብለዋል።
አዲሱ “አንድነት የዘር ብዜት ዩኒዮን” ለክልሉ አርሶ አደር ዘር ማቅረብ ብቻ ሳይኾን ለሌሎች ክልሎችም ጭምር የመሸፈን አቅሙን ማሳደግ እንዳለበት አሳስበዋል።
ይህ ጥረት የሀገራችንን የምርት እና ምርታማነት ዕድገት በማፋጠን የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ መሠረት የሚጥል በመኾኑ የክልሉ የገጠር ክላስተር እና የግብርና ቢሮ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርጉም አረጋግጠዋል።
ዘጋቢ፦ ቴዎድሮስ ደሴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
