
የአማራ ክልል ኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ቢሮ “ኤሌክትሮኒክስ ለዲጂታል 2030 መሠረት” በሚል መሪ መልዕክት በባሕር ዳር ከተማ ከነሐሴ 28 እስከ 30/2018 ዓ.ም ድረስ የሚቆይ የፓናል ውይይት እና አውደ ርዕይ ማዘጋጀቱን አስመልክቶ መግለጫ ሰጥቷል።
መግለጫውን የሰጡት የቢሮው ምክትል ኀላፊ የቻለ ይግዛው የክልሉ መንግሥት የ25 ዓመት አሻጋራ እና ዘላቂ የልማት ዕቅዶች ውስጥ የቴክኖሎጂ ዘርፉ ትኩረት የተሰጠው ጉዳይ መኾኑን ገልጸዋል።
የመርሐ ግብሩ አለማ ቢሮው ባለፉት ሦስት ዓመታት ያከናወናቸውን የዲጂታል ሥራዎችን ማሳየት ነው ብለዋል። በተለይም የሕዝብ አገልግሎት የሚበዛባቸው ተቋማት ላይ ዲጂታላይዜሽንን የማስፋፋት እና ቀልጣፋ አገልግሎት ለሕዝቡ እንዲሳለጥ መደረጉን በመግለጫቸው አንስተዋል።
ባለፉት ሦስት ዓመታት በፍትሕ ሥርዓት፣ በፕሮጀክቶች ክትትል፣ በኢንቨስትመንት እና በግብርና ዘርፎች የዲጂታላይዜሽን ሥራዎች ተከናውነዋል ብለዋል። የዲጂታል ሥራዎች ቀልጣፋ አገልግሎትን በመስጠት ሰዎች ቀሪ ጊዜያቸውን በሌሎች የልማት ተግባራት ላይ እንዲያውሉ የሚያስችል መኾኑንም ተናግረዋል።
በኤግዚቢሽኑ ከ35 በላይ የለሙ እና ችግር ፈች መተግበሪያዎች የሚመረቁ እና የሚጎበኙ እንደኾነም ገልጸዋል።
የሕዝብ አገልግሎት በሚበዛባቸው ተቋማት ተግባራትን ለማሳለጥ ከተከናወኑ አበረታች ጅማሮዎች መካከል “የመሶብ አንድ ማዕከል” ይገኝበታል ያሉት ምክትል ቢሮ ኀላፊው በዚህም ብልሹ አሠራርን የመከላከል ሥራ መሠራቱን አንስተዋል።
ቀጣይነት ባለው መልኩ የቴክኖሎጂ መሠረተ ልማትን በማስፋት የማኅበረሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እንደሚሠራም ጠቁመዋል። መርሐ ግብሩ ከነሐሴ 28/2018 ዓ.ም እስከ 30/2018 ዓ.ም ድረስ ለሦስት ተከታታይ ቀናት እንደሚቆይም ነው የገለጹት።
በሥራውድንቅ ደሳለው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
