“ሰላምን አጥብቆ በመያዝ ምሳሌ እንሁን” የሃይማኖት አባቶች

7
ኢትዮጵያ ለዘመናት ጸንታ የቆመችው በበጎ እና በክፉ ቀናት ተደጋገፎ ባሳለፈው የሕዝቧ ጠንካራ ማኅበራዊ እና መንፈሳዊ እሴት አማካኝነት ነው። እነዚህን ለዘመናት ሀገርን እና ሕዝብን አስተሳስረው ያቆዩ የሰላም እሴቶችን በቃላት ከማስተማር ባሻገር “በተግባር ኖሮ ለሌሎች ምሳሌ መኾን” እንደሚገባ በአማራ ክልል የሚገኙ የሃይማኖት አባቶች አሳስበዋል።
🔗 ከበዓላት፣ ከጋብቻ እና ከሀዘን ጋር የተያያዙ ማኅበራዊ ትስስሮች 🤝 የእርቅ እና የሽምግልና ባሕላዊ እና መንፈሳዊ ሂደቶች፣ 👂በመደማመጥ እና በመመካከር ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ መፍታት ኅብረተሰቡን በአንድነት አስተሳስረው ያቆዩ ዋና ዋና እሴቶች ናቸው። እነዚህ የኢትዮጵያ የሰላም እሴቶች ሕዝቡን በሰላም አስተሳስረው እና የሀገርን አንድነት ጠብቀው የቆዩ ታላላቅ ሀብቶች ናቸው። ሀገር ተገንብታ፣ መንግሥትም ተረጋግቶ እንዲሠራ የእነዚህ እሴቶች ሚናም ከፍተኛ ነበር።
🎙️በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የባሕርዳር ሀገረ ስብከት ዋና ጸሐፊ መልአከ ብርሃን ፍስሐ ጥላሁን “አስታራቂዎች ብፁአን ናቸው፤ የእግዚአብሔር ልጆች ይሰኛሉና” እንደሚለው ቅዱስ ቃሉ ለእርቅ እና ለሰላም ስንቀሳቀስ የእግዚአብሔርን ልጅነት እንደምናገኝ አውቀን ለማስታረቅ ከልብ መንቀሳቀስ አለብን ነው ያሉት።
የሃይማኖት አባቶችም መጽሐፉ የሚለውን ሳይሸራረፉ ማስተማር ብቻ ሳይኾን እኔ ኾኜ አሳይቼ ነው መናገር ያለብኝ በሚለው መርሕ በፍቅር እና በታማኝነት ለአማኞች ምሳሌ መኾን ይገባቸዋል ብለዋል።
የአማራ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት አማካሪ ሼህ ጀውሃር መሐመድ በሃይማኖት መሪዎች ላይ ሰላም ፈላጊነት፣ ታማኝነት እና ሀቀኝነት ጎልቶ መታየት ወሳኝ መኾኑን ገልጸዋል። የሃይማኖት ተቋማት ለሰላም ትልቅ ኀላፊነት አለባቸው፤ የመጀመሪያው ተግባራቸው አማኞቻቸው በሚገኙበት ቦታ ሁሉ የሰላም እና የሥነ ምግባር ትምህርት ማድረስ ነው ብለዋል።
የሰሜን ምዕራብ ኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት ዋና ጸሐፊ መጋቢ ደሳለኝ አባተ የእርቅ እና የአብሮነት እሴቶቻችንን የምናስቀጥላቸው ከውጭ ኾነን በመመልከት ሳይኾን አብሮ ኾኖ በማጋራት እና በመተግበር ነው ብለዋል። የሃይማኖት ተቋማት እና መሪዎች ለሰላም እሴቶች ፍሬያማነት ቀዳሚ ኾነው ሊሠሩ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
💡 ሰላም በቃላት ብቻ የሚገነባ ሳይኾን በተግባር የሚገለጥ እውነታ ነው። ሰላምን በዘላቂነት ለመገንባት ከሚያስፈልጉ ነገሮች አንዱ ደግሞ የአባቶች ምሳሌነት ነው። የሃይማኖት አባቶች በቅድሚያ እራሳቸው የሰላም፣ የእርቅ እና የፍቅር ምሳሌ ኾነው መገኘት ይጠበቅባቸዋል። የሃይማኖት ተቋማት አማኞቻቸውን በሥነምግባር፣ በመደጋገፍ እና በታማኝነት ማነጽ ይኖርባቸዋል።
እሴቶችን ማደስ እና የቆዩትን የእርቅ፣ ሽምግልና እና የመረዳዳት እሴቶች ከወቅቱ ነባራዊ ሁኔታ ጋር በማጣጣም ለቀጣዩ ትውልድ ማስተላለፍ ያስፈልጋል።
📌 የሁሉም ሃይማኖቶች መሠረታዊ አስተምህሮ ሰላም፣ ፍቅር እና አንድነት ነው። ይህንን አስተምህሮ በቃላት ከማስተማር አልፎ በዕለት ተዕለት ሕይወት በመኖር አንዱ የሌላውን ሀዘን እና ደስታ በመጋራት ዘላቂ ሰላምን ዕውን ማድረግ የሁሉም ኀላፊነት ነው።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous article“በጎጃም ያለው ፅንፈኛ ቡድን እየተዳከመና ወደ ተራ ሽፍትነት እየወረደ ነው” ሜጀር ጀኔራል ብርሃኑ ጥላሁን
Next article‎አቢሲኒያ ባንክ በኢትዮጵያ የሰነድ መዋዕለ ነዋዮች ገበያ ላይ ተመዘገበ።