
አቢሲኒያ ባንክ በኢትዮጵያ የሰነድ መዋዕለ ነዋዮች
ገበያ ላይ ተመዝግቧል።
የአቢሲኒያ ባንክ ዋና ሥራ አሥፈጻሚ በቃሉ ዘለቀ ባንኩ በሰነድ መዋዕለ ነዋዮች ገበያ መመዝገቡ ለባንኩ ደንበኞች እና ባለአክሲዮኖች የበለጠ መተማመንን እና ተጠቃሚነትን ከማረጋገጡ ባሻገር ለሀገር ኢኮኖሚ ዕድገት ትልቅ ድርሻ ያበረክታል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ሰነድ መዋዕለ ነዋዮች ገበያ ዋና ሥራ አሥፈጻሚ ጥላሁን እስማኤል (ዶ.ር) አቢሲኒያ ባንክ ለ30 ዓመታት በፋይናንስ ዘርፉ ላበረከተው አስተዋጽኦ አመሥግነዋል። በሰነድ መዋዕለ ነዋዮች ገበያ በመመዝገባችሁ እንኳን ደስ ያላችሁ ብለዋል። አቢሲኒያ ባንክ 6ኛው ተቋም ኾኖ መመዝገቡንም ዋና ሥራ አሥፈጻሚው ገልጸዋል።
የአቢሲኒያ ባንክ ገበያውን መቀላቀል በተቋማት ዘንድ እየጨመረ የመጣውን ዕምነት የሚያሳይ ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ሐና ተኽልቁ ገበያው የአፍሪካ ትልቁ ገበያ የመኾን ዕድሉ ሰፊ ነው፣ ሀገራት በዚህ መሰል ገበያ የፋይናንስ ተቋሞቻቸውን ማሳደግ መቻላቸውንም ጠቁመዋል ።
የብሔራዊ ባንክ ገዢ እዮብ ተካልኝ (ዶ.ር) የሰነድ መዋዕለ ነዋይ ገበያ ዕውን መኾን ኢትዮጵያ ያሳካችው ትልቁ የፋይናንስ ሥርዓት ማሳለጫ ነው ብለዋል።
እስካሁን የተመዘገቡ የፋይናንስ ተቋማትን ያመሠገኑት ገዢው ይህ ትልቅ እርምጃ በመኾኑ እንደ አቢሲኒያ ባንክ ኹሉም ኢንሹራንሶች እና ባንኮች መመዝገብ ይኖርባቸዋል ነው ያሉት።
#አሚኮ #አቢሲኒያ_ባንክ #የሰነድ_መዋዕለ_ነዋዮች_ገበያ #ኢትዮጵያ🇪🇹
#አዲስ_አበባ #ሐምሌ_21_2018_ዓ_ም
ዘጋቢ: ድልነሳ መንግሥቴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
