
በአዲስ አበባ የአፍሪካ ኀብረት አዳራሽ 49ኛው የአፍሪካ ኅብረት የሥራ አሥፈጻሚዎች ምክር ቤት መደበኛ ሥብሠባ በመካሄድ ላይ ይገኛል።
በጉባኤው የተገኙት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጌድዮን ጢሞቲዎስ (ዶ.ር) ኅብረቱ የአህጉሪቱ ዋነኛ ድምጽ እንደመኾኑ መጠን በአሁኑ ወቅት ፈጣን ዕድገት እያስመዘገቡ ካሉ ስምንት የአፍሪካ ሀገራት ተሞክሮ በመነሳት አህጉራዊ ዕድገትን ለማረጋገጥ እና ከዓለም አቀፍ ነባራዊ ሁኔታዎች ጋር ለመራመድ አሠራሩን ሊያስተካክል ይገባል ብለዋል።
ሚኒስትሩ አክለውም ኅብረቱ በጋራ መርህ ላይ የተመሠረተ ዕድገትን ለማረጋገጥ ወሳኝ ሚና መጫወት እንዳለበት አሳስበዋል። የተቋማቱን የፋይናንስ ዘላቂነት ለማረጋገጥ እና ያጋጠሙ ችግሮችን በአስቸኳይ ለመፍታት ቁርጠኛ አቋም ሊኖረው እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
የዘንድሮው ሥብሠባ “የአጀንዳ 2063 ግቦችን ለማሳካት ዘላቂ የውኃ አቅርቦት እና ደኅንነቱ የተጠበቀ የንጽህና አጠባበቅ ሥርዓትን ማረጋገጥ” በሚል መሪ መልዕክ የሚካሄድ ሲኾን ይህም ለአህጉሪቱ ዘላቂ ዕድገት እና ለሕዝቦቿ የጋራ ብልጽግና መሠረት የሚጥል አጀንዳ መኾኑ ተመላክቷል።
የቡሩንዲ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እና የአፍሪካ ኅብረት የሥራ አሥፈጻሚዎች ምክር ቤት ወቅታዊ ሊቀመንበር ኤድዋርድ ቢዚማና አህጉሪቱ የተጋረጡባትን ፈተናዎች አልፋ ስኬት ለማስመዝገብ አሁንም ትልቅ ተስፋ እንዳላት ተናግረዋል።
የአፍሪካ ኅብረት ሊቀመንበር ማህሙድ አሊ የሱፍ አፍሪካውያን በጋራ ድምጽ የአህጉሪቱን ማንነት ለማንጸባረቅ በትብብር መሥራት እንዳለባቸው ገልጸው የተያዙ ሃሳቦችን እና ፖሊሲዎችን ወደ ተጨባጭ ተግባር በመቀየር ረገድ የሚጠበቅባቸውን ኀላፊነት መወጣት እንዳለባቸው አሳስበዋል።
#አሚኮ #AU #ኢትዮጵያ
#አዲስ_አበባ #ሐምሌ_21_2018_ዓ_ም
ዘጋቢ፦ መሠረት መቅጫ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
