በበጀት ዓመቱ የተገኙ ስኬቶችን በማስፋት በቀጣይ የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ በትኩረት መሥራት ይገባል።

6

 

የአማራ ክልል ምክር ቤት የግብርና፣ አካባቢ ጥበቃ እና የውኃ ሃብት ልማት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በስሩ የሚገኙትን የክልሉን ግብርና፣ የመሬት፣ የውኃ እና ኢነርጂ፣ የእንስሳትና ዓሳ ሀብት ልማት ቢሮዎችን፤ የአካባቢና ደን ጥበቃ ባለሥልጣንን፣ የኅብረት ሥራ ኮሚሸን እና የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሸንን የ2018 በጀት ዓመት የዕቅድ አፈፃፀም ገምግሟል። በግምገማው መድረክ የተቋማቱ የሥራ ኀላፊዎች ሪፖርታቸውን አቅርበዋል። ከቋሚ ኮሚቴው አባላት ለተነሱ አስተያየቶች እና ጥያቄዎችም ምላሽ ሰጥተዋል።

የቋሚ ኮሚቴው ሠብሣቢ ከፍያለው ሙላቴ በዚሁ ወቅት:-

✍️ ተቋማቱ ለሠራተኞች ምቹ የሥራ አካባቢ በመፍጠር፣ አሠራሮችን ዲጂታላይዝ በማድረግ የሠሩትን ሥራ በስኬት አንስተዋል።

✍️ የክልሉ ግብርና ቢሮ በ2017/18 የምርት ዘመን የዋጋ ንረትን በማርገብ እና ሀገራዊ የኢኮኖሚ ዕድገትን በመደገፍ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ተናግረዋል። በበጀት ዓመቱ የተሻለ የመስኖ አጠቃቀም፣ የአትክልትና ፍራፍሬ ልማት፣ የግብዓት አቅርቦት እና የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራዎች አበረታች ውጤቶች የተመዘገቡበት ነው።
በጸጥታ ችግር ምክንያት የተዳከመውን የኤክስቴንሽን ሥራ በማነቃቃት ባለሙያዎችን ወደ ሥራ ማስገባት የቀጣይ ትልቁ የቤት ሥራ መኾን እንዳለበትም ቋሚ ኮሚቴው አሳስቧል።

ከፍተኛ ወጭ የወጣባቸው ማዳበሪያዎች እና ምርጥ ዘሮች እንዳይባክኑ መቆጣጠር፣ ከ15 በመቶ ያልበለጠውን የምርጥ ዘር ሽፋን ማሳደግ፣ የአርሶ አደሩን የሜካናይዜሽን ፍላጎት ለማሟላት የባንክ ብድር ማነቆዎችን መፍታት እንደሚገባም ተመላክቷል።

የችግኝ ጣቢያዎችን ደረጃ በማሻሻል በደጋ ፍራፍሬ ራስን መቻል እና የተባይ መከላከያ አሠራርን ማጠናከር ትኩረት ከሚሹ ተግባራት ውስጥ ተጠቅሰዋል።

ግብርናውን ከዝናብ ጥገኝነት ለማላቀቅ እና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ችግር ውስጥ ያሉ መካከለኛ እና ሜጋ የመስኖ ፕሮጀክቶች ቀዳሚ የትኩረት አቅጣጫ ሊኾኑ እንደሚገባ ተመላክቷል።

✍️ በውኃና ኢነርጂ ዘርፍ የውኃ ሽፋን ዕቅድን ለማሳካት የተደረገው ጥረት በጥሩ ሁኔታ ተነስቷል። በሶላር ኢነርጂ የተከናወኑ ሥራዎች እጅግ ውጤታማ ናቸው። በተለይ አርሶ አደሮች የናፍጣ ማሽን መግዣን ወይም ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ታሪፍ ወጭን መቋቋም ስለማይችል የሶላር ቴክኖሎጂ አጠቃቀም ዘላቂ የውኃ አቅርቦትን ለማረጋገጥ ቁልፍ መፍትሔ ኾኖ አገልግሏል።

በበጀት ዓመቱ ይጠናቀቃሉ ተብለው የዘገዩ ፕሮጀክቶችን በቀጣዩ ዓመት ዕቅድ ውስጥ አካትቶ በፍጥነት ማጠናቀቅ ይገባል ተብሏል።

✍️ ቋሚ ኮሚቴው የመሬት ቢሮን አፈጻጸም የገመገመ ሲኾን የሁለተኛ ደረጃ የይዞታ ማረጋገጫ ደብተር በመስጠት እና የመሬት መረጃዎችን ዲጂታላይዝ በማድረግ የሠራው ሥራ በበጎ ተግባር ተነስቷል፤ ይህንኑ የተሻለ አቅም ወደ ከተማ ማምጣት እንደሚያስፈልግም ተመላክቷል።

የካሳ ክፍያ መዘግየት፣ የሙስና ችግሮች እና መሰል ጉዳዮች አፋጣኝ መፍትሄ የሚሹ የመልካም አሥተዳደር እክሎች ናቸው። ከ800 በላይ ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ ወስደው መሬት ያገኙት ከ400 በታች መኾናቸው የመሬት አቅርቦት ክፍተት መኖሩን የሚያሳይ መኾኑን አቶ ከፍያለው ገልጸዋል። በገጠርም ኾነ በከተማ ለኢንቨስትመንት ተብለው የተሰጡ እና ታጥረው ያለልማት የተቀመጡ መሬቶች ላይ ቢሮው በቀጣይ በትኩረት የሚሠራባቸው ኾነው ተጠቁመዋል።

✍️ የእንስሳት እና ዓሣ ሀብት ልማት ቢሮ ዘላቂ የእንስሳት ልማትን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ እንደ ዝርያ ማሻሻያ፣ የሕክምና እና የማድለቢያ ተቋማትን የመሳሰሉ መሠረተ ልማቶችን በጥሩ ደረጃ እየገነባ ይገኛል። በተጨማሪም ይህንን ሥራ ይበልጥ ውጤታማ ለማድረግ ከግብዓት አቅራቢዎች፣ ከዩኒቨርሲቲዎች እና ከተለያዩ ተቋማት ጋር በቅንጅት ለመሥራት የተጀመሩ ጥረቶች ተስፋ ሰጭ መኾናቸው ተገልጿል።

✍️ የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን በተለያዩ ሚዲያዎች፣ ትምህርት ቤቶች እና ሕዝባዊ መድረኮች ግንዛቤ ለመፍጠር እያደረገ ያለው ጥረት እጅግ አበረታች ጅምር ነው። በከተሞች የሚታየውን የደረቅ ቆሻሻ አያያዝ ይበልጥ ለማሻሻል ለዘርፉ ኢንተርፕራይዞች የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባዋል።

በፌዴራል ደረጃ የወጣው የፕላስቲክ አዋጅ በአግባቡ ወደ ተግባር ሊለወጥ ይገባል ብለዋል። እንደ ጣና ሐይቅ ያሉ የውኃ አካላትን ከእንቦጭ አረም ለመጠበቅ ባለሥልጣኑ በትኩረት እንዲሠራ ቋሚ ኮሚቴው አሳስቧል። የዱር እንስሳት እና የተፈጥሮ ጥብቅ ሥፍራዎች አያያዝም ከምንጊዜውም በላይ ተጨማሪ ትኩረት እና እንክብካቤ የሚያሻቸው እንደኾነ ተጠቁሟል።

✍️ በኅብረት ሥራ ልማት ዘርፍ አዳዲስ አባላትን እና ማኅበራትን ማደራጀት፣ የቁጠባ እና ብድር ሥርዓት፣ የገበያ ትስስር፣ የቴክኖሎጂ አጠቃቀም እና የኦዲት ሽፋን ሥራዎች በጥሩ ሁኔታ እየተከናወኑ መኾኑ ተጠቁሟል። በሌላ በኩል የተፈጠረውን የ80 ሚሊዮን ብር የገቢ ጉድለት ወይም ዕዳ ለማስመለስ የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል ተብሏል። ለእረጅም ዓመት ኦዲት ያልተደረጉ ማኅበራት መኖራቸው ተጠቁሞ በትኩረት ሊታዩና ችግር ውስጥ የገቡ ማኅበራትንም ከኪሳራ ለማውጣት አስፈላጊው ርብርብ ሊደረግ ይገባል ተብሏል።

✍️ በአደጋ ስጋት አመራር እና የሰብዓዊ ድጋፍ ሥራዎች ዘርፍ የተጋላጭነት መረጃዎችን ለመሠብሠብ፣ ለሚመለከታቸው አካላት ለማድረስ እና አቅምን ለማሳደግ እየተከናወነ ያለው ሥራ በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ተጠቁሟል። የዕለት ደራሽ ምግብ እገዛ የሚያስፈልጋቸውን ወገኖች በመለየት የተፈቀደውን የዕለት ምግብ አቅርቦት ለሚመለከታቸው ለማድረስ የሚደረገው ጥረት ይበልጥ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል።

በበጀት ዓመቱ መጀመሪያ ላይ ሁሉንም ተፈናቃዮች የማቋቋም ግብ ተይዞ የነበረ ቢኾንም አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ የተፈናቃዮች አኗኗር አሁንም አስቸጋሪ በመኾኑ ማቋቋም እንዳልተቻለ ተገልጿል። በመኾኑም በቀጣዩ በጀት ዓመት በዚህ ረገድ የሚጨበጥ ለውጥ ለማምጣት እና የተፈናቃዮችን ሕይወት ለመቀየር ከፍተኛ ጥረት መደረግ እንዳለበት ተብራርቷል።

በአሁኑ ወቅት የአየር ንብረት ለውጥ ሀገሪቱን ለተለያዩ አደጋዎች እያጋለጠ በመኾኑ ችግሩን ለመሻገር በቅንጅት መሥራት እንደሚገባ ተጠቁሟል። ወደፊት ሊያጋጥም የሚችለው ችግር ዘርፍ ብዙ ሊኾን ስለሚችል እንደየባህሪው ተለዋዋጭ የኾኑ ደራሽ ዕቅዶችን አዘጋጅቶ መንቀሳቀስ እንደሚገባም ቋሚ ኮሚቴው አሳስቧል።

#አሚኮ #ምክርቤት #Ethiopia

#ባሕር_ዳር #ሐምሌ_21_2018_ዓ_ም

በስማቸው አጥናፍ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous article“አፍሪካ ፈተናዎችን ለመቋቋም በራሷ እሳቤ እና ስልት ችግሮቿን መፍታት ይኖርባታል” ጌዲዮን ጢሞቲዮስ (ዶ.ር)
Next articleየጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) መልእክት፦