
የአማራ ክልል ከፍተኛ እና መከካለኛ መሪዎች የ2018 በጀት ዓመት የፓርቲ እና የመንግሥት ሥራዎች አፈጻጸም እና የ2019 በጀት ዓመት የዕቅድ ትውውቅ መድረክ እየተካሄደ ነው።
በመድረኩ ክልሉ በፈተና ውስጥም ኾኖ ውጤታማ የፓርቲ እና የመንግሥት ሥራዎችን ማከናወኑ ተመላክቷል። የክልሉ ፈተና የኾነውን ጽንፈኝነትን በመታገል እና የክልሉን ሰላም ለማረጋገጥ በርካታ ሥራ ተሠርቷል። አሁንም የክልሉን የጸጥታ ችግር በዘላቂነት ለመፍታት በአንድነት መሥራት እንደሚገባ ተነስቷል።
ብልሹ አሠራርን እና ሌብነትን መታገል እንደሚገባም ተገልጿል። ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ መሪዎች በሁሉም ሥራዎች ላይ የጋራ መዳረሻ ርዕይ ይዘው እየሠሩ ነው ብለዋል። የጋራ መዳረሻ ርዕይ ብቻ ሳይኾን የጋራ መግባባት እና ዕውቀት የያዙ ናቸው ነው ያሉት።
ችግሮችን እየተጋፈጡ ውጤት የሚያመጡ መሪዎች መፈጠራቸውን ገልጸዋል። አብዛኛዎቹ መሪዎች መስዋዕትነት እየከፈሉ ለሕዝብ እየሠሩ መኾናቸውንም አንስተዋል። በችግር የማይረበሽ እና ችግሩን የሚጋፈጥ መሪ ተፈጥሯል ነው ያሉት።
በበጀት ዓመቱ ወገንን ያኮራ፤ ጽንፈኛውን ደግሞ ያሳፈረ ስኬታማ ምርጫ በክልሉ መካሄዱን ገልጸዋል። የክልሉ ሕዝብ ለሀገራዊ ምክክር አጀንዳዎችን እንዲያሠባሥብ እና በጉባኤ ላይ ውጤታማ አስተዋጽኦ እንዲያደርግ የተደረገበት ዓመት እንደነበርም ተናግረዋል።
የልማት ሥራዎችን በውጤታማነት ለመፈጸም በርካታ ሥራዎች መፈጸማቸውንም አንስተዋል። በርካታ የታጠቁ ጽንፈኞችን ወደሰላም የመመለስ ሥራ ተሠርቷልም ነው ያሉት።
ጽንፈኛው ቡድን ከሕዝብ መነጠሉንም ገልጸዋል። ሕዝብ የጽንፈኛውን ሀሳብ እና ድርጊት አምርሮ መጥላቱንም አንስተዋል። በርካታ ቁጥር ያላቸው ታጣቂዎች የሰላም አማራጭን ተቀብለው መግባታቸውን ገልጸዋል። የጽንፈኛው መሪዎች የነበሩ የሰላም አማራጭን እየተቀበሉ መኾናቸውን ተናግረዋል።
አሁንም ጽንፈኝነትን የመታገል ሥራችን ይቀጥላል ብለዋል። ብሔርን፣ ሃይማኖትን፣ አካባቢን እና ሌሎችን መነሻ ያደረገን ጽንፈኝነት መታገል እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
የክልሉን አንድነት ለመሸርሸር የሚሠሩ ኀይሎች እንዳሉ ያነሱት ርእሰ መሥተዳድሩ ይሄን አካሄድ አምርሮ መታገል እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
የክልሉን ሕዝብ መብት እና ጥቅም ማስከበር ዋናው ዓላማችን እና ግባችን ነው ብለዋል። የክልሉን አንድነት ማጠናከር፣ በኢኮኖሚም ጠንካራ ማድረግ የሁላችንም ግብ መኾን አለበት ነው ያሉት። የትኛውም አይነት የፖለቲካ አካሄድ ልዩነት ይኑር በሕዝብ መብት እና ተጠቃሚነት ግን በጋራ መቆም አለብን ብለዋል።
መሪዎች ሙስና እና ብልሹ አሠራርን መታገል እንደሚገባቸውም አሳስበዋል። በታጠቁ ጽንፈኞች ላይ አሁንም ሕግ የማስከበር ሥራ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ነው ያሉት። ኀይልን ማሠባሠብ፣ ማጠናከር እና ሰላምን ማረጋገጥ ያስፈልጋልም ብለዋል። ከሕዝብ ሰላም ማስከበር ሥራዎች ባለፈ ሰላማዊ አማራጮች እና ውይይቶች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም አንስተዋል።
ሕገ ወጥ ንግድን፣ እገታን፣ ሕገ ወጥ የመሳሪያ ዝውውርን እና ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውርን መታገል እንደሚገባም ተናግረዋል።
በሁሉም ዘርፍ ምርታመነትን ማሳደግ እና የአገልግሎት ቅልጥፍናን ማሻሻል እንደሚገባም ገልጸዋል። ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ ምርቶችን ማሳደግ ያስፈልጋል ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ የክልሉን የማምረት አቅም በማሳደግ እንደ ሀገር የሚኖረውን አስተዋጽኦ ማሳደግ እንደሚገባም ተናግረዋል።
ዘመናዊ ግብርናን ማሳደግ፣ በአትክልት እና ፍራፍሬ ያለውን አቅም አሟጦ መጠቀም እንደሚገባም ገልጸዋል።
በእንስሳት ሃብት ያለውን እምቅ አቅም መጠቀም እንደሚጠበቅም አንስተዋል። የኢንዱስትሪ ልማትን እና ምርታማነትን ማሳደግ እንደሚገባም ገልጸዋል።
የኮንስትራክሽን ዘርፉን ማሳደግ ግድ እንደሚልም አንስተዋል። በክልሉ የተጀመሩ የልማት ፕሮጄክቶችን በወቅቱ ማጠናቀቅ ይገባልም ብለዋል።
በጸጥታ ችግር አካባቢያቸውን የለቀቁ ባለሀብቶችን መመለስ እንደሚገባም አስገንዝበዋል። የቱሪዝም መዳረሻ ልማትን ማስፋት እና ያለውን አቅም መጠቀም ይገባልም ነው ያሉት።
ትምህርት ላይ በትኩረት መሥራት አለብን ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ የተማረ ዜጋ ተወዳዳሪ ሀገር ይገነባል፤ ባለፉት ዓመታት የተጎዳውን የትምህርት ዘርፍ ማሻሻል እና ውጤታማ ማድረግ አለብን ነው ያሉት። በ2019 የትምህርት ዘመን የታቀደው ሁሉ እንዲሳካ ሁሉም በትኩረት እንዲሠራም አስገንዝበዋል።
የገቢ አሠባሠብ አቅምን ማሳደግ ይገባል፤ ገቢውን ያላሳደገ ክልል ራሱን አይችልም ነው ያሉት። በቅንጅት እና በቁርጠኝነት መሥራት ከቻልን ክልሉን በሁሉም ዘርፍ ማሳደግ እንችላለን፤ የክልሉን ሕዝብ ተጠቀሚነትም እናረጋግጣለን ብለዋል። መሪዎች በቁርጠኝነት እና በቅንጅት እንዲሠሩም አሳስበዋል።
ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
