ለነገዋ ኢትዮጵያ የሚመጥኑ ዩኒቨርሲቲዎችን መገንባት ይገባል።

15
የትምህርት ሚኒስቴር የ2018 ዓ.ም የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎችን የሥራ አፈጻጸም የሚመለከታቸው ባለድርሻ እና አጋር አካላት በተገኙበት እያካሄደ ይገኛል።
ውይይቱ ለነገዋ ኢትዮጵያ የሚገባትን አይነት የከፍተኛ ትምህር ተቋማት መፍጠርን ዓላማ ያደረገ ነው ተብሏል።
በትምህርት ሚኒስትር ​የከፍተኛ ትምህርት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ኮራ ጦሽኔ የአፈጻጸም ግምገማው የመማማሪያ እና የለውጥ ሂደት መጀመሪያ መኾን አለበት ብለዋል።
የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች ከፍተኛ የሕዝብ ሃብት የፈሰሰባቸው ተቋማት እንደመኾናቸው ለተማሪዎች፣ ለቤተሰቦች፣ ለማኅበረሰቡ እና ለሀገሪቱ ትልቅ ኀላፊነት አለባቸውም ነው ያሉት።
በመረጃ የሚመራ ተቋም መገንባት፣ ​የአመራር አፈፃፀም ብቃትን ማሳደግ እና ተጠያቂነትን ከተቋማዊ ነፃነት ጋር አስተሳስሮ መቀጠል ባሕል መደረግ አለበትም ብለዋል።
የ​ከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን ቁጥር ከማሳደግ ወደ ጥራት እና አግባብነት ያለው ተቋም መሸጋገር ወሳኝ እንደኾነም አስገንዝበዋል። አንድን ዩኒቨርሲቲ ስናሻሽል ተቋሙን ብቻ ሳይኾን የብዙ ሺህ ወጣቶችን መጻኢ ዕድል እያሻሻልን መኾኑን ከግምት ውስጥ ማስገባት እንደሚገባም አንስተዋል።
​”ምርምርን ሥናጠናክር ሀገራችን የራሷን ችግሮች የመፍታት አቅሟን ታሳድጋለች” ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው
​የዩኒቨርሲቲ መሪዎችን ስናበቃ ትውልዶችን የሚቀርጽ ተቋምን እያጠናከርን ነው ብለዋል።
​​በመረጃ እና በተጠያቂነት ላይ የተመሠረተ የሥራ ባሕል ስንገነባ ሕዝብ በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ላይ ያለውን ዕምነት እናጠናክራለንም ነው ያሉት።​ ለሦስት ቀናት የሚቆየውን መድረክ በመጠቀም ለዩኒቨርሲቲዎች አዲስ አቅጣጫ መቀየስ፣ በመረጃ የሚመራ፣ በአመራር የሚጠናከር፣ በአፈጻጸም የሚቀጥል ለነገዋ ኢትዮጵያ የሚገባት አይነት ዩኒቨርሲቲዎችን መገንባት እንደሚገባም ሚኒስትር ዴኤታው አሳስበዋል።
በመድረኩ የተለያዩ ጥናታዊ ጽሑፎች የቀረቡ ሲኾን ሰፊ ውይይት ይደረግባቸዋል ተብሎም ይጠበቃል።
ዘጋቢ፦ ቤተልሄም ሰለሞን
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleበአምስት ዓመታት ውስጥ 19 ሚሊዮን የሀገር ውስጥ የሥራ ዕድል ተፈጥሯል።
Next article“የሕዝብን መብት እና ጥቅም ማስከበር የጋራ ግባችን መኾን አለበት” ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ