በአምስት ዓመታት ውስጥ 19 ሚሊዮን የሀገር ውስጥ የሥራ ዕድል ተፈጥሯል።

17
የሥራ እና ክህሎት ሚኒስቴር ባለፉት አምስት ዓመታት ያከናወነውን የልማት ጉዞ የሚገመግም የምክክር መድረክ አካሂዷል። በመድረኩ የሚኒስቴሩ የአምስት ዓመት የለውጥ ጉዞ፣ የተገኙ ውጤቶች፣ ያጋጠሙ ፈተናዎች እና በቀጣይ የሚከናወኑ ሥራዎች ተገምግመዋል።
የሥራ እና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል በአምስት ዓመቱ የልማት ጉዞ በፊት ተበታትነው የነበሩ የተቋሙ አሠራሮች እና እሳቤዎች ወደ አንድ አቅጣጫ መጥተው ዛሬ ለተገኘው ውጤት መሠረት መኾናቸውን ገልጸዋል።
አዲሲቷን ኢትዮጵያ በልጆቿ ሁለተናዊ ትብብር፣ በቴክኖሎጂ ፈጠራ እና በክህሎት ልማት ጉዞ ውስጥ ማየት ይቻላል ያሉት ሚኒስትሯ በቀጣይ የሚኒስቴሩ ትኩረት ከተገኙ ውጤቶች ወደ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት ለመሸጋገር ያግዛል ነው ያሉት።
ሚኒስቴሩ በቀጣይ ዓመታት በአራት ዋና ዋና አቅጣጫዎች ላይ ትኩረት የሚያደርግ ሲኾን የመጀመሪያው የግል ዘርፉን ማብቃት ነው።
የግል ባለሃብቱ በክህሎት ልማት እና በሥራ ዕድል ፈጠራ የበለጠ እንዲሳተፍ የሕግ ማዕቀፎችን እና የዘርፍ ክህሎት ምክር ቤቶችን ማጠናከር ታሳቢ ተደርጓል።
ሁለተኛው አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ እና የወደፊት ክህሎት ላይ ያተኮረ ሲኾን አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን እና የኢንዱስትሪ አቅምን በመጠቀም ዜጎች በዓለም አቀፍ የሥራ ገበያ ተፈላጊ እንዲኾኑ ማስቻል ነው።
ተቋማዊ ራስን መቻል ሦሥተኛው የተቋሙ ትኩረት መኾኑን እና የሥልጠና ተቋማት ከበጀት ጥገኝነት በመላቀቅ በራሳቸው ገቢ እንዲቆሙ፣ በውጤት እና በትርፋማነት እንዲመሩ እና ዓለም አቀፍ ደረጃን እንዲያሟሉ ማድረግ ተጠቃሽ ናቸው።
አራተኛው የሚኒስቴሩ ቀጣይ ትኩረት ደግሞ የዜጎችን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ ተቋም መገንባት እና ተቋሙ በፍጥነት፣ በጥራት እና በውጤታማነት ለዜጎች የሚደርስ አገልግሎት መስጠት እንዲችል ማድረግ ነው።
በትልቁ ማሰብ እና በትንሹ መጀመር የሚለውን መርህ በመከተል ፍጥነትን፣ ጥራትን እና ጠንካራ መሠረትን በማስቀደም ተቋሙ ሀገራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ጥራትን ያማከለ የዜጎች ተስፋ ተቋም ለመኾን እየሠራ እንደኾነም ተጠቁሟል። በዚህም የሥራ ጥራት ማረጋገጫ ሥርዓቱ ከዓለም አቀፍ ተቋም ሰርተፊኬት ማግኘቱንም ሚኒስትሯ ገልጸዋል።
በአምስት ዓመቱ 19 ሚሊዮን የሀገር ውስጥ የሥራ ዕድል የተፈጠረ ሲኾን ይህም የዕቅድ አፈጻጸሙ 97 በመቶ መኾኑ ተገልጿል።
በተጨማሪም ባለፉት አምስት ዓመታት ከ1 ነጥብ 6 ሚሊዮን በላይ ዜጎችን በውጭ የሥራ ስምሪት ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉ ተጠቁሟል።
ዘጋቢ፦ አየለ መስፍን
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous article“ታጣቂዎች በመጠለያነት የያዟቸውን ትምህርት ቤቶች ለቀው ይውጡልን” የተማሪ ወላጆች
Next articleለነገዋ ኢትዮጵያ የሚመጥኑ ዩኒቨርሲቲዎችን መገንባት ይገባል።