
ትምህርት ቤት የተስፋ መነሻ፣ የነገው ትውልድ ሳይንስ እና ጥበብ የሚቀሰምበት የዕውቀት መገብያ ስፍራ ነው።
ኾኖም በአማራ ክልል በተፈጠረው የሰላም አለመረጋጋት ምክንያት ታጥቀው ጫካ የገቡ ኀይሎች የሕጻናትን የመማሪያ ክፍሎች ለወታደራዊ መጠለያ እና ለጦር ካምፕነት በመጠቀማቸው የመማር ማስተማር ሂደቱ ተስተጓጉሎ ቆይቷል።
በዚህም ምክንያት የነገው ሀገር ተረካቢ የኾኑ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ታዳጊዎች ከትምህርት ገበታቸው ተፈናቅለው ላለፉት ሦሥት ዓመታት ቤታቸው ለመቀመጥ ተገደዋል።
ታጣቂ ኀይሉ በክልሉ ታዳጊዎች ላይ እየፈጸመ ያለው ይህ ዘመን አይሽሬ በደል የብዙዎችን ህሊና የሚያም ሲኾን ዕውቀት ለማካፈል የተዘጋጁ መምህራንም በደኅንነት ስጋት ምክንያት ያለ ሥራቸው በቤት ውስጥ እንዲቀመጡ አድርጓል።
ዛሬም ድረስ በርካታ የገጠር ትምህርት ቤቶች የታጣቂ ኀይሎች መጠለያ ካምፕ ኾነው መቀጠላቸውን በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች የሚገኙ ነዋሪዎች ይናገራሉ።
የምሥራቅ ጎጃም ዞን ነዋሪዎች በአካባቢያቸው የሚገኙ የገጠር ትምህርት ቤቶች የታጣቂዎች መጠለያ ኾነው እያገለገሉ ነው ብለዋል።
በዚህም በትምህርት ቤቱ አገልግሎት ይሰጡ የነበሩ የልጆቻቸው መቀመጫ ወንበር፣ ጥቁር ሰሌዳ እና ሌሎች ቁሳቁሶች ከጥቅም ውጭ እንዲኾኑ እና እንዲዘረፉ ኾነዋል ነው ያሉት።
የደቡብ ጎንደር ዞን ነዋሪዎች በበኩላቸው ታጣቂ ኀይሉ በአካባቢያቸው የሚገኙ የገጠር ትምህርት ቤቶችን እንደ መጠለያነት እና ወታደራዊ ካምፕ እየተገለገሉበት መኾኑንም ጠቁመዋል።
የትምህርት ቤቶች ግቢም ዳዋ ውጧቸው እንደሚገኙ ትዝብታቸውን ለአሚኮ ገልጸዋል። “ትምህርት ቤቶች ከፊታችን ለሚመጣው አዲሱ የትምህርት ዘመን ለማስተማር ዝግጁ መኾን አለባቸው፤ የታጣቂ ኀይሉ የይዞታ ሰፈር ሊኾኑ አይገባም፤ ልጆቻችን ለአራተኛ ዓመት ከትምህርት ገበታ መራቅ የለባቸውም፤ የጫካው ኀይል በመጠለያነት የያዛቸውን ትምህርት ቤቶች ለቆ ይውጣ፤ በልጆቻችን የነገ ዕጣ ፈንታ መቀለዱን ያቁም ” ሲሉም ነዋሪዎቹ በምሬት ጥሪያቸውን አቅርበዋል።
ባለፉት ሦሥት ዓመታት በክልሉ የተፈጠረው የሰላም አለመረጋጋት በመማር ማስተማር ሂደቱ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማስከተሉን የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኀላፊ ጥላሁን ወርቅነህ አንስተዋል።
በክልሉ የተሟላ ሰላም ባለመኖሩ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሕጻናት ከትምህርት ገበታቸው መራቃቸውን ነው የገለጹት።
ትምህርት በተቋረጠባቸው ራቅ ያሉ ገጠራማ የክልሉ አካባቢዎች ትምህርት ቤት እንዲከፈትላቸው እና ልጆቻቸው እንዲማሩ በተደጋጋሚ ሲጠይቁ መቆየታቸውንም ጠቁመዋል።
በ2019 የትምህርት ዘመን ላለፉት ሦሥት ዓመታት የተዘጉ ትምህርት ቤቶች ከየትኛውም አካል ነጻ ኾነው የመማር ማስተማር ተግባሩን እንዲጀምሩ ጥረት እየተደረገ መኾኑንም ቢሮ ኀላፊው ተናግረዋል።
በአማራ ክልል በ2019 የትምህርት ዘመን ከቅድመ አንደኛ እስከ ሁለተኛ ደረጃ የትምህርት እርከኖች ከ7 ነጥብ 6 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎችን ለመመዝገብ መታቀዱን ከክልሉ ትምህርት ቢሮ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።
ታዋቂ ግለሰቦች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ምሁራን እና መላው ማኅበረሰብ «አንድም ተማሪ ከትምህርት ገበታ ውጭ እንዳይኾን» የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡም ተቋሙ ጥሪ አቅርቧል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
