
የምሥራቅ ዕዝ ዞብል ክፍለ ጦር “የጀግኖችን መስዋዕትነት እየዘከርን አደራቸውን ከግብ እናደርሳለን” በሚል መሪ ቃል አምስተኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን አክብሯል።
በምስረታ በዓሉ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት የክፍለ ጦሩ አዛዥ ኮሎኔል ጀማል አማን እንዳሉት ክፍለ ጦሩ ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ እስከ አሁን ባለው የትግል ጉዞው የሕዝብን እና የሀገርን ሉዓላዊነት ለመጠበቅ አርዓያነት ያለው ታሪክ መሥራቱን ገልጸዋል። አሁንም የጠላትን ሃሳብ በማምከን ሕዝባዊ አደራውን በብቃት በመወጣት ላይ ይገኛል ነው ያሉት።
የምስረታ በዓሉን ስናከብር ጀግኖች ለሀገር አንድነት የከፈሉትን መስዋዕትነት በመዘከር ለቀጣዩ ትውልድ ታሪክን በአግባቡ ማስተላለፍ ይገባል ብለዋል። ክፍለ ጦሩ ከምስረታው ማግስት የክፍሉ የሠራዊት አባላት በከፈሉት መስዋዕትነት ያስመዘገበውን አንጸባራቂ ድል ዛሬም በጸረ ሽምቅ ውጊያ ሕግን በማስከበር ግዳጁን በጽናትና በጀግንነት እየተወጣ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።
የክፍለ ጦሩ ምክትል አዛዥ ለውጊያ ድጋፍ ሌተናል ኮሎኔል አይቸው ወንድሜነህ በከፍተኛ የግዳጅ ዝግጁነት ተልዕኮውን እየፈጸመ የሚገኘው የዞብል ክፍለ ጦር፤ የድሉ መሠረት የኾነውን ሕዝባዊ ባህሪያት በመተግበር ግዳጁን በብቃት ለመወጣት በሚያስችለው አስተማማኝ ቁመና ላይ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።
ክፍለ ጦሩ የምስረታ በዓሉን በሚያከብርበት ዕለት በእሁዲት የሚገኙት የሠራዊት አባላት ለተማሪዎች የመማሪያ ቁሳቁስ ድጋፍ በማድረግ ሕዝባዊ አለኝታነታቸውን ማሳየታቸውን የገለጸው ደግሞ በአካባቢው የሚገኘው ሬጅመንት አዛዥ መቶ አለቃ እዮብ ማሞ ነው።
በዕለቱ የክፍለ ጦሩን አመሠራረት እና የአምስት ዓመታት የአውደ ውጊያ ውሎ በጽሑፍ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል። የክፍሉ የአውደ ውጊያ ውሎ በአግባቡ ተሰንዶ ለአሁኑ ትውልድ መቅረቡ ጀግኖች የፈጸሙትን ድንቅ ገድል ከመዘከር ባለፈ በቀጣይ የላቀ ጀግንነትን ለመሥራት ወኔን የሚሰንቅ መኾኑንም የክፍሉ አባላት ተናግረዋል።
መረጃው የምሥራቅ ዕዝ ነው።
