ከተባበርን አፍሪካን መቀለብ እንችላለን።

6
🇪🇹
የማንኛውም ሀገር ሉዓላዊነት፣ ክብር እና ብሔራዊ ጥቅም ሊከበር ብሎም ሊጠበቅ የሚችለው በውስጣዊ አንድነት ላይ የተመሠረተ ጠንካራ መሠረት ሲኖር ነው።
የውስጥ ሰላም እና አንድነት ሳይረጋገጥ የውጭ ተጽዕኖን መቋቋምም ኾነ ብሔራዊ ጥቅምን ማስከበር አይቻልም።
ብሔራዊ ጥቅም የሚረጋገጠው በውስጣዊ ጥንካሬ፣ በኢኮኖሚ አቅም፣ በዲፕሎማሲያዊ ብስለት እና በጠንካራ የመከላከያ ኃይል አጠቃላይ ውህደት ነው።
የታሪክ እና የባሕል ተመራማሪ ፕሮፌሰር አሕመድ ዘካሪያ ኢትዮጵያዊያን ሀገራቸውን በታሪክ ለዘመናት ሉዓላዊነቷን በመጠበቅ የአፍሪካ የዲፕሎማሲ ቁንጮ እንድትኾን በማስቻል፤ በአፍሪካ ተደማጭነቷን በማጉላት ውጤታማ ማድረግ የቻሉት በውስጣዊ አንድነታቸው መኾኑን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያን ጸጋ ለይቶ በመረዳት፤ አውቆ በመጠቀም፤ ልማት ላይ ውጤታማ ተሳትፎ በማድረግ፤ ፖለቲካዊ ችግሮችን በምክክር በመፍታት፤ ውስጣዊ አንድነትን በመፍጠር የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ማረጋገጥ ይገባል ብለዋል።
ያለፉት መንግሥታት በሥልጣን ዘመናቸው የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ለማስከበር መሥራታቸውን አንስተዋል። አሁን ላይ ብሔራዊ ጥቅምን ለማሳደግ በተሠራው ተግባር የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እና ተደማጭነት እያደገ መምጣቱንም ተናግረዋል።
የሕዳሴ ግድብ የኢትዮጵያዊያን አንድነት ማሳያ መኾኑንም አንስተዋል። ግጭት የኢኮኖሚ ኪሳራን፣ የኑሮ ውድነትን እና ማኅበራዊ ቀውስን የሚያስከትል ከመኾኑም ባለፈ የቴክኖሎጂ ተደራሽነት እና የኢንዱስትሪ ውጤታማነትን እና ሁሉን አቀፍ የሀገር ዕድገትን የሚጎዳ ነውም ብለዋል።
ጎራ ይዞ የሚደረግ የፖለቲካ መጎዳዳት ብሔራዊ ጥቅምን አያረጋግጥምም ነው ያሉት። በመኮራረፍ የሚደረግ ጉዞ ኢትዮጵያን እንደማያሻግርም ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች እርስ በዕርስ ግጭትን በመፍጠር ሀገርን ለማዳከም እየሠሩ መኾኑን ተናግረዋል። ዓባይን የጋራ ቀይ ባሕርን ለብቻ የሚል አካሄድን በመጠቀም ኢትዮጵያ ተጠቃሚ እንዳትኾን እየሠሩ መኾኑንም አንስተዋል።
ውስጣዊ አንድነትን በማረጋገጥ፤ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ እና የማኅበራዊ ችግሮችን በውይይት በመፍታት የጠላቶችን ሤራ ማክሸፍ ይገባልም ብለዋል።
ኢትዮጵያ ለአፍሪካ አንድነት የምታከናውነውን ተግባር ማስቀጠል እንደሚገባትም አሳስበዋል። ከተባበርን አፍሪካን መቀለብ እንችላለን ነው ያሉት። በአንድነት በመቆም ከኢትዮጵያ አልፎ ቀጣናዊ አንድነትን መፍጠር ያስፈልጋልም ብለዋል።
ግጭቶችን በማስቀረት እና ውስጣዊ አንድነትን በማጠናከር ብሔራዊ ጥቅምን ማረጋገጥ የትውልዱ ወሳኝ ተግባር መኾኑንም ተናግረዋል።
✍️ዘጋቢ:- ያየህ ፈንቴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleችግሮችን አልፎ ለፍጻሜ የበቃው የአስፋልት መንገድ
Next articleጀግኖች ለሀገር አንድነት የከፈሉትን መስዋዕትነት በመዘከር ለቀጣዩ ትውልድ ታሪክን ማሳተላለፍ ይገባል።