
በሰሜን ጎጃም ዞን የጎንጅ ቆለላ (ኮሬ – አዲስ ዓለም) የ10 ነጥብ 74 ኪሎ ሜትር አስፋልት መንገድ ፕሮጀክት 10 ነጥብ 59 ኪሎ ሜትር የሚኾነው መጠናቀቁን የኢትዮጵያ መንገዶች አሥተዳደር አስታውቋል።
የመንገድ ፕሮጀክቱ አጠቃላይ አፈጻጸም 98 ነጥብ 82 በመቶ መድረሱም ተገልጿል።
የመንገዱ ሥራ የካቲት/2012 ዓ.ም ነበር የተጀመረው። በሦሥት ዓመት ለማጠናቀቅም ታቅዶ ነበር።
እንደ አካባቢው ሁኔታ የመንገድ ስፋቱ በገጠር 10 ሜትር፣ በቀበሌ 12 ሜትር እና በወረዳው ከተማ 21 ነጥብ 5 ሜትር ኾኖ እየተገነባ መቆየቱም ተጠቅሷል።
አሁን ላይ የጠረጋ፣ የአፈር ቆረጣ እና ሙሌት፣ የሰብ ቤዝ፣ የቤዝ ኮርስ እና ሙሉ የ10 ነጥብ 74 ኪሎ ሜትር የአስፋልት ንጣፍ ሥራዎች ሙሉ በሙሉ ተጠናቅቀዋል ብሏል የኢትዮጵያ መንገዶች አሥተዳደር።
ከቀሪ ሥራዎች አኳያ የፍሳሽ ማስወገጃ ቦዮች 98 ነጥብ 58 በመቶ፣ የእግረኛ መንገድ እና የመንገድ ምልክት ሥራዎች 50 በመቶ ላይ እንደሚገኙም አመላክቷል።
ቫትን ጨምሮ ከ333 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት እንደተመደበለት የተገለጸው ይህ የመንገድ ፕሮጀክት ግንባታ ኅብር ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን በግንባታ እና የአማካሪነት ሚናውን ደግሞ ሃይዌይ ኢንጂነርስ ኤንድ ኮንሰልታንትስ ኀላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር እያከናወኑት ይገኛሉ።
አሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ያነጋገራቸው የጎንጅ ቆለላ ነዋሪ እና የመንገድ ፕሮጀክቱ የማኅበረሰብ ተወካይ ላቀው ንጋቱ መንገዱ በ3 ዓመታት ጊዜ ውስጥ እንዲጠናቀቅ ታስቦ የተጀመረ ቢኾንም በበጀት እጥረት፣ በሀገራዊ ጉዳዮች እና በጸጥታ ችግር ለ6 ዓመታት ያህል ሲጓተት መቆየቱን አስታውሰዋል።
አሁን ላይ ደግሞ የአስፋልት ሥራዎች ተጠናቀው የዜብራ፣ የትራፊክ ምልክቶች እና የቀለም ቅብ ሥራዎች ሲከናወኑ መመልከታቸውን ነግረውናል።
የመንገዱ መጠናቀቅ ከዚህ ቀደም ይባክን የነበረውን ከፍተኛ የትራንስፖርት ወጭ፣ ሰዓት እና እንግልት የሚያስቀር በመኾኑ የአካባቢው ማኅበረሰብ በእጅጉ ተደስቷልም ብለዋል።
አካባቢው ከፍተኛ የምርት ቀጣና በመኾኑ የመንገዱ መጠናቀቅ ለአርሶ አደሮች የገበያ ትስስር የሚፈጥር፣ ባለሀብቶችን የሚስብ እና ሌሎች ልማቶችን እና አካባቢውን የሚያነቃቃ እንደኾነም አስረድተዋል።
በቀጣይም ጎንጅ ቆለላን ከደቡብ ጎንደር ዞን ጋር የሚያገናኘው የማኅበረሰብ የመንገድ ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኝም ጠይቀዋል።
ፕሮጀክቱ ጥቅምት/2019 ዓ.ም ሙሉ በሙሉ ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
