
የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ትምህርት መምሪያ በ2019 የትምህርት ዘመን በብሔረሰብ አሥተዳደሩ በሚገኙ 11 ወረዳዎች እና የከተማ አሥተዳደሮች ከ264 ሺህ በላይ ተማሪዎችን ለመመዝገብ አቅዶ ወደ ተግባር መግባቱን ገልጿል።
የመምሪያ ኀላፊው ሰይፈ ሞገስ እንዳስታወቁት የምዝገባ ሂደቱ የጸጥታ ችግር ባሉባቸው እንደ ጻግቭጅ፣ አብርገሌ፣ ወፍላ፣ ዛታ እና ኮረም ባሉ ወረዳዎችም ጭምር እየተከናወነ ይገኛል።
እስከ አሁን ከ86 ሺህ በላይ ተማሪዎች የተመዘገቡ ሲኾን ወላጆች እስከ ነሐሴ 30/2018 ዓ.ም ድረስ ዕድሜያቸው ለትምህርት የደረሱ ሕጻናትን ቀድመው እንዲያስመዘግቡ ጥሪ አቅርበዋል።
አቶ ሰይፈ ትምህርት የወደፊት ሀገር ተረካቢዎች የሚታነጹበት ተቋም በመኾኑ ከፖለቲካ ነፃ በኾነ መንገድ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
በተመሳሳይ በሰቆጣ ከተማ አሥተዳደር በሚገኙ 17 ትምህርት ቤቶች በቅድመ መደበኛ ዘርፍ ብቻ ከ3 ሺህ በላይ ተማሪዎችን ለመመዝገብ ታቅዶ ወደ ተግባር መገባቱን የከተማው ትምህርት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ክብሩይስፋ መለሰ ገልጸዋል።
በአዝባ አንደኛ እና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ልጆቻቸውን ሲያስመዘግቡ አሚኮ ያገኛቸው ወላጆች በበኩላቸው ልጆቻቸውን በወቅቱ ማስመዝገባቸው መጻሕፍት እና ሌሎች ድጋፎችን ቀድመው እንዲያገኙ እንደረዳቸው ተናግረዋል።
ዘጋቢ፦ ደጀን ታምሩ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
