
የሀረሪ ክልል መሥተዳድር ምክር ቤት ካቢኔ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አስተላልፏል።
መሥተዳድር ምክር ቤቱ በቅድሚያ የተወያየው የሀረሪ “የመሶብ” የአንድ ማዕከል ዲጂታል የመንግሥት አገልግሎት ድርጅታዊ መዋቅር እና የሰው ኀይል ፍላጎት በተመለከተ በቀረበ ረቂቅ ላይ ነው።
ረቂቁም የሀረሪ መሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት በተለያዩ የመንግሥት ተቋማት የሚሰጡትን አገልግሎት በአንድ ቦታ በማሠባሠብ፣ በማደራጀት እና ዲጂታላይዝ በማድረግ ተገልጋዩ ላልተፈለገ እንግልት እና ወጭ ሳይጋለጥ ተደራሽ፣ ግልጽ፣ ቀልጣፋ፣ ወጭ ቆጣቢ እና ውጤታማ አገልግሎት በመስጠት እርካታን ለማሳደግ ያለመ መኾኑ ተጠቁሟል።
መሥተዳድር ምክር ቤቱም ድርጅታዊ መዋቅር ላይ በሰፊው ከመከረ በኋላ በሙሉ ድምጽ አጽድቆታል።
ካቢኔው በመቀጠል የተወያየው በሐረሪ ከተማ ማዘጋጃ ቤት ለከንቲባ ኮሚቴ ውሳኔ የቀረበ የአደረጃጀት ማሻሻያ ረቂቅ ላይ ነው።
የአደረጃጀት ማሻሻያውም ማዘጋጃ ቤቱ በሕግ የተሰጠውን ኀላፊነት በአግባቡ ለማከናወን የሚያስችለውን አደረጃጀት በመፍጠር የሚስተዋሉ ችግሮችን በመቅረፍ ውጤታማ የኾኑ ተግባራትን እንዲያከናውን ለማስቻል መኾኑ ተገልጿል።
ካቢኔውም በማሻሻያው ላይ በጥልቀት ከተወያየ በኋላ በሙሉ ድምጽ አጽድቋል።
መሥተዳድር ምክር ቤቱ ከዚህ በተጨማሪም በሌሎች አጀንዳዎች ዙሪያ ውይይት በማካሄድ ውሳኔ አስተላልፏል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
