
የሀገር መከላከያ ሠራዊት ዞብል ክፍለ ጦር በምዕራብ ጎጃም ዞን ሰከላ ወረዳ ከሃይማኖት አባቶች፣ ከሀገር ሽማግሌዎች እንዲሁም ከትምህርት መስክ ተወካዮች ጋር ወቅታዊ የአካባቢው ሰላምን በተመለከተ የውይይት መድረክ አካሂዷል።
በመድረኩ የተገኙት የዞብል ክፍለ ጦር አዛዥ ኮሎኔል ጀማል አማን እንዳሉት በወረዳው ሠራዊቱ እና የክልሉ የፀጥታ ኃይል በሠራዉ የተቀናጀ ስምሪት በአካባቢው ሰላም እንዲሰፍን ማስቻሉን ጠቅሰዋል። ሀገርን ከዘመን ጋር ለማስቀጠል የተማረ ትውልድ እንደሚያስፈልግም አስገንዝበዋል።
በትምህርት ሂደት መስተጓጎል ሳቢያ የሚፈጠረውን የትውልድ ክፍተት ሁሉም አካል ቆም ብሎ ሊያስብበት እና ለመፍትሔው በጋራ ሊሠራ ይገባልም ብለዋል።
ማኅበረሰቡ በተለይም የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች በተሳሳተ አላማ ጫካ የገቡ አካላትን ከመንግሥት አካላት ጋር ተቀራርበው ሰላማዊ ውይይት ማድረግ እንዲችሉ የበኩላችሁን ጥረት ማድረግ እንደሚገባቸውም አዛዡ መልእክት አስተላልፈዋል።
የሰከላ ወረዳ ተወካይ አሥተዳዳሪ ሃይማኖት ሙሉ የወረዳው ሰላም አሁን ወዳለበት ደረጃ እንዲደርስ የተሠራዉ ሥራ እጅግ ከፍተኛ እንደነበር ጠቁመዋል። በወረዳው በሰፈነው አንጻራዊ ሰላም ተጀምረው የነበሩ መሰረተ ልማቶች በጥሩ የአፈጻጸም ደረጃ መቀጠላቸውን ተናግረዋል።
በወረዳው አንጻራዊ ሰላም መስፈን ቢችልም የትምህርት ሂደቱ ግን በሚፈለገው ደረጃ መቀጠል እንዳልቻለ ጠቁመዋል። ታጣቂዎች በሚያደርጉት ግላዊ አላማን የማሳካት ጉዞ የነገው ሀገር ተረካቢ ትውልድ ላይ አሉታዊ ተጽእኖ እያደረሰ መኾኑን መገንዘብ እና ከዚህ ድርጊት መቆጠብ ይገባል ብለዋል።
የመድረኩ ተሳታፊዎች በበኩላቸው ወረዳው አሁን ያለበት የሰላም ሁኔታ የተሻለ መሆኑን አንስተው የቀጣዩን ዓመት ትምህርት ለማስጀመር አካባቢው የበለጠ ሰላማዊ እንዲኾን የበኩላችንን ድርሻ ለመወጣት ዝግጁ መኾናቸውን አረጋግጠዋል።
ዘገባው የምስራቅ ዕዝ ነው
