“የኢትዮጵያን ዕምቅ አቅሞች በመግለጥ ረገድ ግለሰቦች የማይተካ ሚና አላቸው” ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመሥገን ጥሩነህ

8

 

ባሕር ዳር፡ሚያዚያ 18/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመሥገን ጥሩነህ በአብዲ ነጋሽ ቅርስ ማሰባሰቢያና ማስጎብኛ ቤት ተገኝተው የቅርሶችን ስብስብ ከተመለከቱ በኃላ የሚከተለውን መልእክት አስተላልፈዋል፦

ኢትዮጵያ የረጅም ዘመናት ሥልጣኔና የጥንታዊ ቅርሶች ባለቤት መሆኗን የምንመሰክረው እንደ አቶ አብዲ ዓይነት የትውልድ አሻራ ጠባቂዎችን ስንመለከት ነው።

አብዲ ነጋሽ ቅርስ ማሰባሰቢያና ማስጎብኛ ቤት ተገኝተን የጎበኘነው የቅርሶች ስብስብ፣ ለሀገራችን ታሪክና ባሕል ትልቅ ክብር የሚሰጥ ድንቅ ሥራ ነው።

እነዚህ ሃብቶች፣ አሁን በሚመጥናቸው ታሪካዊ ሥፍራ ተደራጅተው ለዕይታ መብቃታቸው ለዘርፉ ትልቅ እመርታ ነው። ትውፊታዊ ቅርሶቹ ባለፈውና በሚመጣው ትውልድ መካከል የቆሙ ህያው ድልድዮች ናቸው።

የኢትዮጵያን እምቅ አቅሞች በመግለጥ ረገድ ግለሰቦች የማይተካ ሚና አላቸው። እንደ አቶ አብዲ ዓይነት በፍላጎት እና በሀገር ፍቅር ስሜት የሚሠሩ ሰዎች ደግሞ የዜጋን አስተዋጽዖ ይበልጥ ከፍ ያደርጋሉ።

የአቶ አብዲ የቅርሶች ስብስብ የከተማችን አንዱ የቱሪስት መስሕብ ሆኗል። የቅርስ ዜጋዊ ዲፕሎማሲ ማሳያም ነው። አያሌ የሀገር ውስጥና የውጭ ቱሪስቶች በየጊዜዉ ይጎበኙታል።

እንዲህ ያሉ የሀገር መዝገቦችን በታሪካዊ ሕንጻዎች ውስጥ ጠብቆ ማቆየት፣ ለብልጽግና የምናደርገውን ጉዞ በዕውቀትና በማንነት ላይ ለመገንባት የሚያግዘን ተደማሪ ዐቅም ነው።

የመደመር መንግሥት እንደነዚህ ያሉ የግል ጥረቶችን በማበረታታትና የታሪክ ሥፍራዎችን መልሶ በማልማት፣ ቅርሶቻችን የኢኮኖሚ ምንጭና የሀገር ኩራት እንዲሆኑ የጀመረውን ሥራ አጠናክሮ ይቀጥላል። ተቋማትና ሀገር ወዳድ ዜጎች እንደ አቶ አብዲ ያሉ ታታሪዎችን እንዲደግፉ ጥሪ አቀርባለሁ።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/Amharamediacorporations

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየንግድ ቤቶችን ለመከራየት የሚከፈል የቁልፍ ክፍያ ያስጠይቃል?