
የተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ የያዳም ፋውንዴሽን መስራች እና የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ደመቀ መኮንንን የዓለም አቀፉ የተመጣጠነ ምግብ አቅርቦት ማስፋት ንቅናቄ (SUN) መሪ ቡድን አባል አድርገው ሾመዋል።
ዋና ፀሐፊው የአቶ ደመቀ ልምድ እና አመራር ለመሪ ቡድኑ ሥራ እንዲሁም ለንቅናቄው ግቦች መሳካት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ተናግረዋል።
አቶ ደመቀ በዋና ፀሐፊው የተሾሙት በምግብ ዋስትና እና በተመጣጠነ ምግብ አቅርቦት ዘርፍ ላበረከቱት የላቀ አስተዋጽኦ እውቅና በመስጠት ነው።
ዋና ጸሐፊው የአቶ ደመቀ ሹመት ከኅዳር 2019 ዓ.ም እስከ ታህሳስ 2021 ዓ.ም. እንደሚቆይ አስታውቀዋል።
አቶ ደመቀ አባል ሆነው የተሾሙበት የንቅናቄው መሪ ቡድን በዓለም አቀፍ ደረጃ የተመጣጠነ ምግብ አቅርቦት እንዲኖር ለሚደረገው ጥረት ስትራቴጂካዊ አመራር እና ክትትል የሚሰጥ ነው።
67 አባል ሀገራት እና 4 የሕንድ ግዛቶች ብሔራዊ የምግብ እና የሥርዓተ-ምግብ ዕቅዶቻቸውን እንዲያሳኩ ድጋፍ ያደርጋል።
የአቶ ደመቀ ሹመት ንቅናቄው ከእ.አ.አ 2026 እስከ 2030 ስትራቴጂካዊ ማዕቀፍ ትግበራን በሚጀምርበት ወሳኝ ወቅት መሆኑ በደብዳቤው ተመላክቷል።
ማዕቀፉ በምግብ አመራረትና አቅርቦት ሥርዓት ሽግግር፣ በአየር ንብረት ለውጥ መከላከል እንዲሁም በግጭት እና በችግር ውስጥ ለሚገኙ ሀገራት የሚሰጠውን ድጋፍ ማጠናከርን ጨምሮ የተቀናጁ አካሄዶችን መፍጠር ላይ ዋና ትኩረቱን አድርጓል።
ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ በደብዳቤው ላይ ባሰፈሩት መልዕክት፣ ውስብስብ እና በፍጥነት በሚለዋወጠው ዓለም አቀፋዊ ሁኔታ ውስጥ የስርዓተ ምግብ ጉዳይ ቅድሚያ የሚሰጠው አንገብጋቢ ጉዳይ መሆኑን ገልጸዋል።
ግጭቶች፣ የአየር ንብረት ጫናዎች እና እየቀነሰ የመጣው የልማት ዕርዳታ በተለይም በጣም ተጋላጭ በሆኑ ሀገራት የምግብ ዋስትና እና የተመጣጠነ ምግብ አቅርቦት ላይ ከፍተኛ ጫና እያሳደሩ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል።
እነዚህን ተግዳሮቶች በመቋቋም እና የተመጣጠነ ምግብ ጉዳይ በልማት አጀንዳ ግንባር ቀደም ጉዳይ ሆኖ እንዲቀጥል በማድረግ ረገድ በሀገራት የሚመራ እና በርካታ ባለድርሻ አካላትን የሚያሳትፍ አካሄድ ወሳኝ ሚና እንዳለው ዋና ጸሐፊው አመልክተዋል።
ዋና ጸሐፊው የአቶ ደመቀ ልምድ እና አመራር ለመሪ ቡድኑ ሥራ እንዲሁም ለንቅናቄው ግቦች መሳካት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ያላቸውን ሙሉ እምነት ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ መድረኮች ያላት ተሰሚነትና ተፅዕኖ ፈጣሪነት እየጨመረ ሲሆን፣ በዚህም የተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማትን የሚወክሉ ኢትዮጵያዊያን ቁጥር እያደገ ነው።
#የመደመር_መንግሥት!
#ትልቅ_ሀገር_ትልቅ_ሕዝብ_ታላቅ_ርዕይ!
Ameco #BloodCovenant #PriceOfFreedom
#EthiopiaSovereignty
#ባሕር_ዳር #ኅዳር_12_2019_ዓ_ም
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
