‎ከ210 ሺህ ኩንታል በላይ ጥራቱን የጠበቀ ሰሊጥ ለማዕከላዊ ገበያ ቀረበ።

24

‎በአማራ ክልል ምዕራብ ጎንደር ዞን በመተማ ወረዳ በኮኪት አንደኛ ደረጀ የገበያ ማዕከል የሰሊጥ አቅራቢ ነጋዴ ሀሰን ተገኘ ከባለፈው ዓመት የተሻለ ግብዓት መኖሩን ገልጸዋል። የዘንድሮ ሰሊጥ ከባለፈው ዓመት የተሻለ ጥራት ስላለው ተፈላጊነቱ መጨመሩንም አንስተዋል።
‎
‎እስካሁን ከ20 ሺህ ኩንታል በላይ ሰሊጥ ግብይት በመፈፀም ለማዕከላዊ ገቢያ ማቅረባቸውንም አቶ ሀሰን ተናግረዋል።
‎
‎በገበያ ማዕከሉ ግዥ እየፈጸሙ የሚገኙት “የታደሰ ገበየሁ ኤም ኤስ ኤ ዘይት ማቀናበሪያ ፋብሪካ ድርጅት ተወካይ አቶ ታደሰ አስፋው በበኩላቸው የዚህ ዓመት የሰሊጥ ምርት ጥራት እና ግብዓት ከባለፈው ዓመት ወቅት ጋር ሲነጻጸር እጅግ የተሻለ መኾኑን ነው የገለጹት።
‎
‎ድርጅቱ በዚህ ዓመት ለማዕከላዊ ገበያ የሚቀርበውን የሰሊጥ ምርት በብዛት በመግዛት ምርቱን ወደ ውጭ ኤክስፖርት እንደሚያደርግም ነው ያነሱት።
‎
‎እስካሁንም ከ7 ሺህ ኩንታል ያላነሰ ሰሊጥ ግዥ መፈጸሙንም ተናግረዋል።
‎
‎በምዕራብ ጎንደር ዞን በበጀት ዓመቱ ከ1 ሚሊዮን 370 ሺህ ኩንታል በላይ የሰሊጥ ምርት ለማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብ ታቅዶ እየተሠራ መኾኑን የዞኑ ንግድ እና ገበያ ልማት መምሪያ አስታውቋል።
‎
‎ከታቀደው መካከል ከ1ሚሊዮን 300 ሺህ ኩንታል በላይ የሚኾን ምርት ለውጭ ኤክስፖርት፤ ከ58 ሺህ 800 ኩንታል በላይ የሚኾነው ምርት ደግሞ ለሀገር ውስጥ ኢንዱስትሪዎች የሚውል ነው።
‎
‎በምዕራብ ጎንደር ዞን የንግድ እና ገበያ ልማት መምሪያ ተወካይ ኀላፊ እና የግብይት ባለሙያው ጌታቸው ኃይሌ ለአሚኮ እንደገለጹት እስካሁን በ18 አንደኛ ደረጃ የገበያ ማዕከላት የሰሊጥ ምርት ግዥ እየተፈጸመ ነው።
‎
‎በዞኑ 154 አቅራቢዎች፣ በውል እርሻ እና ኢንቨስትመንት ዘርፍ የተሰማሩ እና የላኪ ፈቃድ ያላቸው ባለሃብቶች እንዲሁም የኅብረት ሥራ ማኅበራት ግዥ እየፈጸሙ ይገኛሉ።
‎
‎በዚህ ዓመት ሁሉም የውል እርሻ አስመራቾች ልክ እንደ አቅራቢዎች እና እንደ አቀነባባሪዎች 1ኛ ደረጃ ገብተው ያስመረቱትን ምርት እዲረከቡ እና ግብይት እንዲፈጸሙ እየተደረገ ነው፡፡
‎
‎በዚህ ዓመት ከጥቅምት ወር ጀምሮ በተደረገ የሰሊጥ ግብይት እስካሁን 210 ሺህ ኩንታል በላይ ጥራቱን የጠበቀ ሰሊጥ ለማዕከላዊ ገበያ መቅረቡንም አቶ ጌታቸው ገልጸዋል።
‎
‎በዞኑ ባለፈው ዓመት ከ468 ሺህ 800 ኩንታል በላይ የሰሊጥ ምርት ለማዕከላዊ ገበያ መቅረቡን ከመምሪያው የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
‎
‎#የመደመር_መንግሥት!
‎
‎#ትልቅ_ሀገር_ትልቅ_ሕዝብ_ታላቅ_ርዕይ!🇪🇹
‎
‎#ባሕር_ዳር #ኅዳር_12_2019_ዓ_ም
‎
‎ዘጋቢ፦ ቴዎድሮስ ደሴ
‎
‎የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous article‎ለ36 ሺህ ሰዎች የገበያ ዕድል የሚያሰፋው የማር ኤግዚቢሽን በደሴ ከተማ እየተካሄደ ነው።
Next article‎🩸 የደም ቃል ኪዳን፦ የማይደፈረው የክብር መቅደስ!